ስምምነቱ ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
ስምምነቱ ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ ያስችላል
ደሴ ፤ ታህሳስ 1/2018(ኢዜአ)፡- በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና በአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት ዘላቂ ሰላም በማስፈን የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ልማቶችን ለማካሄድ የሚያስችል መሆኑን የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።
ከደሴ ከተማ ነዋሪዎች መካከል መቶ አለቃ ጌቱ አበበ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ለዘመናት የገነባናቸው የአብሮነት፣ የፍቅር፣ የመቻቻልና የመከባበር የጋራ እሴቶቻችንን በማስቀጠል ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ ከሁላችንም ይጠበቃል ብለዋል።
መንግስት ሰላምን ለማጽናትና ልማትን ለማስቀጠል የሰጠው ትኩረት የሚደነቅ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና በአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት መካከል የተደረሰው ስምምነትም ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና ልማትን ለማስቀጠል የሚያስችል መሆኑን ጠቁመው፤ ስምምነቱ ለህዝቡ እፎይታን በመስጠት ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጡ ልማቶችን ለማካሄድ ያስችላል ብለዋል።
የከተማው ነዋሪ አቶ ኢብራሂም አሊ በበኩላቸው፣ የከተማዋን ሰላም በጋራ በማጽናት የተጀመሩ ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሁለንተናዊ ተሳትፏችንን እንቀጥላለን ብለዋል።
ስምምነቱ ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ ከማስቻሉ ባለፈ ለሌሎችም ትምህርት የሚሆን ነው ብለዋል።
የችግሮች መፍቻ የሆኑ እሴቶችና ባህሎችን በማጎልበት ለንግግርና ለውይይት ቅድሚያ በመስጠት ሰላም እንዲሰፍን ኃላፊነታችን እንወጣለን ያሉት ደግሞ መምህር አሸናፊ ጸጋዬ ናቸው።
የውጭና የውስጥ ጠላቶቻችን በተቀነባበረ መንገድ ግጭት እንዲባባስ የሚያደርጉትን ጥረት በጋራ ማክሸፍ ይገባናል ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ሰሚራ ሰይድ ናቸው።
ሰሞኑን በተፈጠረው የሰላም ስምምነት እጅግ መደሰታቸውን ጠቁመው፤ ስምምነቱ ለሌሎችም ትምህርት የሰጠና መለመድ ያለበት መሆኑን ገልጸዋል።
ታላቅ የሰላም ጥሪን ያነገበ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰላማዊ ሰልፍ በደሴ ከተማ መካሄዱ ይታወሳል።