ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ኮፕ- 32 እንድታስተናግድ መመረጧ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የሚያስችሉ ስራዎች ውጤታማነትን የሚያመላክት ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 1/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ 32ኛውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ጉባኤን (ኮፕ- 32) እንድታስተናግድ መመረጧ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የሚያስችሉ ስራዎች ውጤታማነትን የሚያመላክት መሆኑን በኢትዮጵያ የጀርመን ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚ ፈርዲናንድ ቮን ዌይህ (ዶ/ር) ገለጹ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት በ2011 ዓ.ም የተጀመረው የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአካባቢ ስነ-ምኅዳር ደኅንነት በማስጠበቅ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

ይህን ተከትሎ ኢትዮጵያ በብራዚል ቤለም በተካሄደው የዓለም የአየር ንብረት (COP-30) ጉባኤ ላይ 32ኛውን የዓለም የአየር ንብረት (COP-32) ጉባኤ ለማስተናገድ መመረጧ ይታወቃል።

በኢትዮጵያ የጀርመን ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚ ፈርዲናንድ ቮን ዌይህ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት በኢትዮጵያ በሀይድሮ የኤሌትሪክ ሀይል፣ አረንጓዴ አሻራና ሌሎች በአረንጓዴ ልማት በተሰሩ ስራዎች ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም እያከናወነች የምትገኘው ተግባር ችግሩን ለመከላከል ያላትን ቁርጠኝነት እንደሚያመላክትም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ዘርፍ ፣ በታዳሽ ሀይል እና በደን ልማት የተሰሩ ውጤታማ ስራዎች ኢትዮጵያ የኮፕ-32 ጉባኤን እንድታስተናግድ ለመመረጧ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸዋል።

በሀገሪቱና በዓለም አቀፍ ደረጃ በተካሄዱ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤዎች ኢትዮጵያ የነበራት ጉልህ ተሳትፎ ለመመረጧ ካገዟት መስፈርቶቹ መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በጀርመን የልማት እቅድ የግብርና ዘርፍ ዋና ምስሶ መሆኑን ገልጸው፤ ለዘርፉ ውጤታማነት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚከናወኑ ስራዎች ትኩረት ከሚደረግባቸው ስራዎች መካከል እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።

ጀርመን በኢትዮጵያ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን እየደገፈች እንደምትገኝ ገልጸው፤ ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም