አርሶአደሮች በኩታ ገጠም ካለሙት የስንዴ ልማት የተሻለ ምርት ለማግኘት በትኩረት እየሰሩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አርሶአደሮች በኩታ ገጠም ካለሙት የስንዴ ልማት የተሻለ ምርት ለማግኘት በትኩረት እየሰሩ ነው
ሮቤ፤ ታህሳስ 01 /2018 (ኢዜአ)፡- በኩታ ገጠም ካለሙት የስንዴ ልማት የተሻለ ምርት ለማግኘት ጠንክረው እየሰሩ መሆናቸውን የባሌ ዞን የአጋርፋና ሲናና ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።
በዞኑ በመኽር ሰብል ከለማው ከ528 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ከ19 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
በባሌ ዞን አጋርፋ ወረዳ የአሊ ቀበሌ አርሶ አደር ጫላ ደሞ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በኩታ ገጠም ተደራጅተው ካለሙት 23 ሄክታር የስንዴ ልማት የተሻለ ምርት ይጠብቃሉ።
ለስራውም ውጤታማነት የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የሙያ ድጋፍና ምርጥ ዘር አቅርቦት አድርጎላቸው የስንዴ ልማቱ በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በጥሩ ቁመና ላይ ከሚገኘው ሰብልም ከሄክታር እስከ 75 ኩንታል ምርት ለማግኘት ማቀዳቸውን አስታውሰዋል።
በኩታ ገጠም ያለሙትን ስንዴ የአረምና የተባይ ቁጥጥር በማድረግ ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እየሰሩ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የአጋርፋ ወረዳ አርሶ አደር መንግስቱ ኤጄሬ ናቸው።
በምርት ዘመኑ በመስመር የመዝራትና የተሻሻሉ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረጋቸው ከአንድ ሄክታር ከ70 ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።
የሲናና ወረዳ አርሶ አደር ሁሴን በከር በበኩላቸው፤ የግብርና ባለሙያዎች ምክርን ተግባራዊ በማድረግ አምና በባቄላ የሸፈኑትን የእርሻ ማሳ ሰብልን በማፈራረቅ የሰብል በሽታ መቆጣጠር መቻላቸውን ተናግረዋል።
ዘንድሮ በስንዴ በመቀየራቸው የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።
የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሙአዊያ ፉአድ በበኩላቸው እንዳሉት፤ በዞኑ በመኽሩ የምርት ወቅት በተለያዩ የሰብል ዘሮች የለማው ከ528 ሺህ ሄክታር መሬት እንክብካቤ እየተደረገለት ነው።
በዘር ከተሸፈነው ማሳ ውስጥም 427 ሺህ ሄክታሩ በመስመር መዝራትን ጨምሮ ሌሎች የተሻሻሉ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ በኩታ ገጠም የተሸፈነ ነው ብለዋል።
በዘር የተሸፈኑት እነዚህ ማሳዎች ለምግብ፣ ለኢንዱስትሪ ግብአትና ለኤክስፖርት የሚውሉ የግብርና ምርቶች ላይ በማተኮር እየተከናወነ ነው ብለዋል።
በዘንድሮ የምርት ወቅት ከ19 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት መታቀዱንም ምክትል ኃላፊው አመልክተዋል።