በክልሉ ለአደጋዎች ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ለአደጋዎች ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ ነው
ሰመራ፤ ታህሳስ 1/2018(ኢዜአ)፡-በአፋር ክልል ለሚከሰቱ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ መሆኑን የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በቅርቡ ለከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በሰጡት ስልጠና ላይ እንዳስገዘቡት ምርታማነትን በማሳደግ ተረጂነትን ዜሮ ለማድረሰ በቁርጠኝነትና በቅንጅት መስራት ይገባል ብለዋል።
ክልሎች ደግሞ የሰው ሰራሽም ሆነ የተፈጥሮ አደጋዎች ሲከሰቱ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የራስ አቅምን ያገናዘበ ስራ በመስራት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የአፋር ክልል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሸነር አቶ አካደር ኢብራሂም እንዳሉት፤ በክልሉ ለሚከሰቱ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አቅሞች ተፈጥረዋል።
በዚህም መሰረት በክልሉ በ26 ወረዳዎች ኮሚቴ በማቋቋምና ንቅናቄ በመፍጠር ገቢ የሚሰበሰብበት አሰራር ተዘርግቶ እየተተገበረ መሆኑን ተናግረዋል።
አደጋ ሲከሰት በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት ከሚያስችሉ ዝግጅቶች መካከል አንዱ የእርሻ ስራን ማስፋፋት እንደሆነ ጠቅሰው፤ በዚህም 1 ሺ 802 ሄክታር መሬት በተለያየ ዘር ተሸፍኖ እየለማ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ይህንን ለማከናወን የሚያስችል 97 መጋዘኖች ተጠናቀው አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።
የህብረተሰቡ የእርስ በእርስ የመረዳዳት ባህል ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማሳሰብ ሌሎች አደረጃጀቶችንም በመጠቀም የሰብአዊ ድጋፍ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።