ቀጥታ፡

የመደመር መንግሥት የብዝሃ ኢኮኖሚ እሳቤ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ተወዳዳሪ አልሚዎችን እያፈራ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 1/2018(ኢዜአ)፡-የመደመር መንግሥት የብዝሃ ኢኮኖሚ እሳቤ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ተወዳዳሪ አልሚዎችን እያፈራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ለኢዜአ እንደገለጹት፤ መንግሥት ለኢንዱስትሪ ልማት የሰጠው ትኩረት ዘርፉ በእጅጉ እንዲነቃቃና እመርታዊ ለውጥ እንዲያመጣ አስችሏል።

ለአብነትም የፖሊሲ ለውጥ፣ የስትራቴጂ እና የተቋማትን ቅንጅታዊ አሰራር የሚያጠናክሩ የማሻሻያ ስራዎችን ጠቅሰዋል።

በማሻሻያዎቹ በመታገዝ የኢንዱስትሪ ምርታማነትን ለመጨመርና የአምራች ዘርፉን እድገት በቀጣይነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስኬቶች መመዝገባቸውን ነው ያነሱት። 

በዋናነት የብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ልማት ተግባራዊ መደረጉ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እንዲጨምርና የልማት ስራው አካል እንዲሆን አስቻይ ሁኔታ መፍጠሩንም አብራርተዋል።

ይህም የግሉ ዘርፍ ለአሰራር ስርአቶች ያለው ግንዛቤ እንዲዳብርና ከመንግስት ጋር ተቀራርቦ እንዲሰራ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አክለዋል።

የተገኘው ስኬት የመደመር መንግስት የብዝሃ የኢኮኖሚ እሳቤ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ተወዳዳሪ አልሚዎችን እያፈራ ስለመሆኑ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል ብለዋል።     

በኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻልና የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቀነስ አዎንታዊ ሚና እንዳላቸው ሚኒስትሩ አክለዋል።

ከግብዓትና ከኃይል አቅርቦት ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ውስንነቶችን ለማረም የተከናወኑ ተግባራት ለኢንዱስትሪ ምርታማነት መጨመር ጉልህ ፋይዳ እያበረከቱ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

የሀገር ውስጥ ምርት ፍላጎትን ለመጨመርና የማምረቻ ወጪን ለመቀነስ የተሰሩ ስራዎች የዜጎችን ተጠቃሚነት እያረጋገጡ መምጣታቸውን አስታውቀዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም