ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለስደተኞች መጠለያና ድጋፍ ለመስጠት ያላት ቁርጠኝነት እውነተኛ የአጋርነት ተግባር  ነው 

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 1/2018(ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ስደተኞች መጠለያና ድጋፍ ለመስጠት ያሳየችው ቁርጠኝነት እውነተኛ የአጋርነት ተግባር  ማሳያ ነው ሲሉ የዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) የኢትዮጵያ ዋና ልዑክ አቢብቱ ዋኔ ገለጹ::

በዓለም አቀፍ ደረጃ የስደተኞች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ አሁን ላይ በዓለም ላይ 90 ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞችና ተፈናቃዮች ይገኛሉ።

ከዚህ ቁጥር ውስጥ አብዛኛዎቹ ስደተኞችና ተፈናቃዮች የሚገኙት በአፍሪካ ሀገራት ነው፡፡

በኢትዮጵያም ከተለያዩ ጎረቤት ሀገራት የመጡ በርካታ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች የሚገኙ ሲሆን ከዚህ ቀደም ለስደተኞቹ ከለላ ለመስጠት የሚያስችሉ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።

ይህ ተግባር ኢትዮጵያን በአፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ስደተኞችን ከሚያስተናግዱ ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ ከማድረግ ባለፈ በተደጋጋሚ ጊዜያት ዓለም አቀፍ እውቅናና አድናቆት እንድታገኝ አስችሏታል።

የዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) የኢትዮጵያ ዋና ልዑክ አቢብቱ ዋኔ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ስደተኞችን የመቀበል ባህሏ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ከመፈረም በላይ የሄደ ነው።

ኢትዮጵያ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ስደተኞችን በመቀበል በአጋርነት እየደገፈች እንደምትገኝም ጠቅሰዋል። 

ስደተኞቹ ጥበቃ፣ የዕለት ተዕለት ኑሮ ማገዣ እና የጤና አገልግሎት ማግኘት እንዳለባቸው ገልጸው ኢትዮጵያ ይህንን ጥበቃ ለመስጠት የተቻላትን ሁሉ እያደረገች መሆኑን አረጋግጠዋል።

ይህ ተግባር ሀገሪቱ ለሰው ልጅ ክብር እና ደህንነት የመቆሟን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ስደተኞችን መቀበል ብቻ ሳይሆን፣ በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ለማዋሃድ ትልቅ እርምጃ እየወሰደች እንደምትገኝ አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለስደተኞቹ አስፈላጊውን ድጋፍና እርዳታ ለመስጠት እንደ ዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅትና የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን ካሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በቅርበት እየሠራች እንደሆነ አስታውቀዋል።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ስደተኞችን በማስተናገድ አርአያ የሆነ ተግባር እያከናወነች እንደምትገኝ አቢብቱ ዋኔ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም