ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ መድን ከሸገር ከተማ ጋር ተስተካካይ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 1/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሶስተኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሃ ግብር ኢትዮጵያ መድን ከሸገር ከተማ ይጫወታሉ።

ጨዋታው ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይካሄዳል።

ኢትዮጵያ መድን በሊጉ ካደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች መካከል ሁለቱን ሲያሽንፍ ሶስት ጊዜ ደግሞ ተሸንፏል። በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ ላይ ስድስት ግቦችን ሲያስቆጥር ሰባት ጎሎችን አስተናግዷል። 

የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ መድን በዘጠኝ ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዟል። ቡድኑ ባለፉት ሶስት የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም።

ሸገር ከተማ በበኩሉ በሊጉ ካከናወናቸው ስምንት ጨዋታዎች መካከል በሶስቱ ድል ሲቀናው ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። ሶስት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል። ዘጠኝ ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያገናኝ ሰባት ግቦች ተቆጥረውበታል።

አዲስ አዳጊው ሸገር ከተማ በ12 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል።

ጨዋታው ኢትዮጵያ መድን ወደ አሸናፊነት መንገድ ለመመለስ ሸገር ከተማ ደግሞ በአሸናፊነቱ ለመቀጠል የሚያደርጉት ነው።

መርሃ ግብሩ ኢትዮጵያ መድን በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ከግብጹ ፒራሚድስ ጋር በነበረው የማጣሪያ ጨዋታ ምክንያት የተራዘመ መሆኑን የሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም