ተጠባቂው የሪያል ማድሪድ እና የማንችስተር ሲቲ የሻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያ - ኢዜአ አማርኛ
ተጠባቂው የሪያል ማድሪድ እና የማንችስተር ሲቲ የሻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 1/2018(ኢዜአ)፡- በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዛሬ ዘጠኝ ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ምሽት 5 ሰዓት ላይ ሪያል ማድሪድ እና ማንችስተር በበርናባው ስታዲየም የሚያገናኘው ጨዋታ የእግር ኳስ ቤተሰቡን ትኩረት ስቧል።
ሪያል ማድሪድ በ12 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ማንችስተር ሲቲ በ10 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ሁለቱ ክለቦች በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊጉ ሲገናኙ የአሁኑ ለ15ኛ ጊዜ ነው።
ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 14 ጨዋታዎች ማንችስተር ሲቲ አምስት ጊዜ ሲያሸንፍ ሪያል ማድሪድ አራት ጊዜ ድል ቀንቶታል። በቀሪ አምስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
ሁለቱም ቡድኖች በጨዋታዎቹ ላይ በተመሳሳይ 24 ግቦችን አስቆጥረዋል።
ቡድኖቹ በሻምፒዮንስ ሊጉ ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት እ.አ.አ በ2024/25 የውድድር ዓመት ነው። በጥሎ ማለፉ ተገናኝተው ሪያል ማድሪድ ማንችስተር ሲቲን 3 ለ 1 አሸንፏል።
የስፔኑ ቡድን 15 ጊዜ ውድድሩን በማሸነፍ በስኬት ያሸበረቀ ታሪክ አለው። ማንችስተር ሲቲ አንድ ጊዜ ዋንጫ አንስቷል።
ሪያል ማድሪድ እና ማንችስተር ሲቲ ባለፉት ዓመታት በአውሮፓ መድረክ እያደረጉት ያለው ፉክክር የዛሬውን ጨዋታ ትኩረት እንዲያገኝ አድርጎታል።
በሌሎች መርሃ ግብሮች ክለብ ብሩዥ ከሊግ ፎርማቱ መሪ አርሰናል፣ አትሌቲኮ ቢልባኦ ከወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ፒኤስጂ፣ ጁቬንቱስ ከፓፎስ፣ ቤኔፊካ ከናፖሊ፣ ባየር ሌቨርኩሰን ከኒውካስትል ዩናይትድ እና ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ከቦዶ ግሊምት በተመሳሳይ ከምሽቱ 5 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ምሽት 2 ሰዓት ከ45 ካራባግ ከአያክስ እና ቪያሪያል ከኮፐንሃገን ይጫወታሉ።