የወላይታ የዘመን መለወጫ በዓል "ጊፋታ" በዓለም ቅርስነት ተመዘገበ - ኢዜአ አማርኛ
የወላይታ የዘመን መለወጫ በዓል "ጊፋታ" በዓለም ቅርስነት ተመዘገበ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 1/2018(ኢዜአ)፡- ጊፋታ የወላይታ ሕዝብ የአዲስ ዓመት ፌስቲቫል በሰው ልጆች ወካይ ቅርስነት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ተመዘገበ፡፡
በሕንድ፣ ኒው ዴልሂ እየተካሄደ በሚገኘው 20ኛው የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰሱ የባሕል ቅርሶች ጥበቃ ኮሚቴ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ያቀረበችው የወላይታ የዘመን መለወጫ በዓል "ጊፋታ" በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል።
"ጊፋታ" በወላይታ ዘንድ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው ታላቅ በዓል ሲሆን፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ የሕዝቡ የማንነት መገለጫ የሆነ የአሮጌው ዓመት ማብቂያና የአዲሱ ዓመት መጀመሪያ የመሸጋገሪያ በዓል ነው፡፡
ጊፋታ ዕድሜ፣ ጾታ፣ ሃይማኖት ወይም ሌላ ማኅበራዊ ደረጃ ሳይለይ ለሁሉም ሠላም እና ማኅበራዊ ትሥሥር አስተዋጽኦ በማድረግ በዩኔስኮ የተለዩትን ዘርፎች ያካተተ ሁሉን አቀፍ ተግባራትን በማበረታታት የሚከበር በዓል መሆኑ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ አስችሎታል።