ቀጥታ፡

የሳይበር ጥቃቶችን በመከላከል ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 1/2018(ኢዜአ)፡- በቁልፍ መሠረተ-ልማቶች ላይ የሚቃጡ ዓይነተ-ብዙ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎችን በማክሸፍ ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር(ኢመደአ) አስታወቀ።

በአስተዳደሩ የሳይበር መከላከል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር መሐመድ ፈረጃ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በያዝነው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሦስት ወራት 13ሺህ 443 ጥቃቶችና የጥቃት ሙከራዎች ተመዝግበዋል።

ከሙከራዎቹ መካከልም ከፍተኛውን መጠን የያዘው ‘ሰርጎ ገብ’ የተሰኘው የሳይበር ጥቃት መሆኑን ገልጸው፤ ይህም በድረ ገጽ፣ በቁልፍ መሠረተ-ልማቶች እና ሌሎች ዘርፎች ላይ ዒላማ ያደረጉ እንደነበርም አስረድተዋል።

በመሆኑም በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር እና ቁልፍ መሠረተ-ልማቶቹን በሚያሥተዳድሩ ተቋማት ጥረት 97 ነጥብ 16 በመቶ ለሚሆኑት የጥቃት ሙከራዎች ምላሽ ተሰጥቷል ብለዋል።

በዚህም መሠረት የሳይበር ጥቃቶቹን በመቆጣጠር፣ የጉዳት መጠንን በመቀነስ፣ ድጋሚ ለጥቃት እንዳይጋለጡ ደኅንነታቸውን የማጠናከር ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።

የሳይበር ጥቃት ሙከራዎቹ ቢሳኩ እንደሀገር ይደርስ የነበረው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑንም ነው አቶ መሐመድ ፈረጃ የተናገሩት።

በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር እና በቁልፍ መሠረተ-ልማቶቹ አሥተዳዳሪ ተቋማት የጋራ ጥረት በርካታ ጥቃቶችን መከላከል መቻሉን ጨምረው ገልጸዋል።

በቀጣይም በሀገር ላይ የሚቃጡ የሳይበር ጥቃቶችን ለመከላከል ቅንጅታዊ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም