ቀጥታ፡

የአንጎል ዕጢ በሽታ እና መደረግ ያለባቸው ጥንቃቄዎች

ኒዩሮ ሰርጂን እና የሕጻናት የነርቭ ቀዶ ሕክምና ሰብ ስፔሻሊስት ዶክተር ያሬድ ንጉሴ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ከአንጎል ዕጢ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ሙያዊ ገለጻ አድርገዋል።

👉 የአንጎል ዕጢ ምልክቶች

ዕጢው እንደተከሰተበት የአንጎል ክፍልና ያለበት የህመም ደረጃ ምልክቶቹ እንደሚለያዩ ዶክተር ያሬድ አስገንዝበዋል። በዚህም መሠረት፡-

• የራስ ህመም (Headache) (በጣም ጠንካራ እና በተደጋጋሚ የሚስተዋል)፤

• የሚጥል በሽታ (Seizures)፤

• የዐይን የማየት ዐቅም መቀነስ፤

• የማሰብ እና የማስታወስ ችግሮች (ቀላል ነገሮችን መርሳት፣ ትኩረት ማድረግ አለመቻል)፤

• የሰውነት ክፍል አለመታዘዝ (ለምሳሌ አንድ እጅ ወይም እግር አለመንቀሳቀስ)፤

• ለመናገር መቸገር (ቃላትንበትክክል መናገር አለመቻል) እንዲሁም

• የፀባይ ለውጥ መኖር(ያልተለመደ ስሜታዊነት፣ ብስጭት) እና መሰል ምልክቶች ሲስተዋሉ ወደ ሕክምና ተቋም በመሄድ ተገቢውን ምርመራ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

👉 የአንጎል ዕጢ ታማሚ ማድረግ ያለበት ጥንቃቄ እና ሕክምናው

የሕክምና ባለሙያው እንዳሉት፤ አንድ ሰው በሕክምና ምርመራ የአንጎል ዕጢ እንዳለበት ሲረጋገጥ መደናገጥ የለበትም። የሕክምና ሂደቱን ግን በጥብቅ መከታተል ይጠበቅበታል። በዚህም መሠረት፡-

• የሕክምና ባለሙያን ምክር በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ፤

• ሕክምናው እንደ ዕጢው ዓይነት እና የህመም ደረጃ እንደሚወሰን አስገንዝበዋል። በመሆኑም የመድኃኒት (Chemotherapy)፣ የጨረር እና የቀዶ ጥገና ሕክምናዎች እንደ ሁኔታው እንደሚሰጡ አብራርተዋል።

• ጤናማ አመጋገብ እና የኑሮ ዘይቤን መከተል፤ አካላዊ እንቅስቃሴ ማዘውተር፤ አልኮልና ሲጋራ ከመጠቀም መቆጠብ እንዲሁም እየወሰዱ ከሆነ ማቆም፤

• ሁሌም አዎንታዊ አስተሳሰብን ማስቀደም፤ በዚህ ህመም ተይዘው በሕክምና ከተረዱ በኋላ ጤናማ ሆኖ መኖር እንደሚቻል መገንዘብ ይገባል ይላሉ ባለሙያው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም