ሊቨርፑል ኢንተር ሚላንን አሸነፈ - ኢዜአ አማርኛ
ሊቨርፑል ኢንተር ሚላንን አሸነፈ
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 30/2018(ኢዜአ)፦ በአውሮፓ ሊግ ሻምፒዮንስ ሊግ ተጠባቂ ጨዋታ ሊቨርፑል ኢንተር ሚላንን 1 ለ 0 አሸንፏል።
ማምሻውን በጁሴፔ ሜኤዛ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ዶምኒክ ስቦዝላይ በ88ኛው ደቂቃ የማሸነፊያውን ጎል በፍጹም ቅጣት ምት አስቆጥሯል።
ጨዋታው ተመጣጣኝ ፉክክር ተደርጎበታል።
ውጤቱን ተከትሎ ሊቨርፑል በ12 ነጥብ ደረጃውን ወደ ስምንት ከፍ አድርጓል።
ኢንተር ሚላን በተመሳሳይ 12 ነጥብ በግብ ክፍያ በልጦ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በሌላኛው ጨዋታ አትላንታ ቼልሲን 2 ለ 1 አሸንፏል። ጂያንሉካ ስካማካ እና ቻርልስ ዲ ኬቴላሬ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
ጆአኦ ፔድሮ ለቼልሲ ብቸኛውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ቶተንሃም ሆትስፐርስ ስላቪያ ፕራግን 3 ለ 0 አሸንፏል። መሐመድ ኩዱስ፣ ዣቪ ሲመንስ እና የስላቪያ ፕራጉ ዴቫድ ዚማ በራሱ ላይ ግቦቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
ጁል ኩንዴ ባስቆጠራቸው ግቦች ባርሴሎና ከመመራት ተነስቶ ኢንትራክት ፍራንክፈርትን 2 ለ 1 አሸንፏል። አንስጋር ናውፍ ለጀርመኑ ቡድን ብቸኛውን ጎል ከመረብ ጋር አገናኝቷል።
በሌሎች ጨዋታዎች አትሌቲኮ ማድሪድ ፒኤስቪ አይንድሆቨንን እና ማርሴይ ዩኒየን ሴንት ጊሎይስን በተመሳሳይ 3 ለ 2 ሲያሸንፉ ሞናኮ ጋላታሳራይን 1 ለ 0 ረቷል።
ዛሬ አስቀድመው በተደረጉ ጨዋታዎች ባየር ሙኒክ ስፖርቲንግ ሊዝበንን 3 ለ 1፣ ኦሎምፒያኮስ ካይራት አልማቲን 1 ለ 0 አሸንፈዋል።