ቀጥታ፡

የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ስኬታማ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 30/2018 (ኢዜአ):- በኦሮሚያ ክልል ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ስኬታማ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት አወሉ አብዲ ገለጹ።   

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አወሉ አብዲ በክልሉ ሰሜን ሸዋ ዞን ደብረሊባኖስ ወረዳ በኩታ ገጠም በመኸር እርሻ የለማ ስንዴ  አጨዳ እንዲሁም በዋጫሌ ወረዳ የመስኖ ስንዴ የመዝራት ስራን አስጀምረዋል።


 

ምክትል ፕሬዝዳንት አወሉ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የተሻሻሉ የግብርና መሳሪያዎችንና የተሟላ ግብዓት በመጠቀም አርሶ አደሮች ምርታቸውን ከአገር አልፎ ለውጭ ገበያ ማቅረብ መጀመራቸው የሚበረታታ ነው።

በክልሉ ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎችን በመጠቀም የተሰሩ ስራዎች ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ትልቅ ውጤት ማስገኘታቸውን ገልጸዋል።

በዚህም በግብርናው ዘርፍ በመታገዝ ከተረጂነት በመላቀቅ እንዲሁም በምግብ ዋስትና ራስን በመቻል ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚያስችል እመርታ ማስመዝገብ መቻሉን አመልክተዋል።

በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ በማምረት ትልቅ ውጤት መገኘቱን ጠቅሰው፤ በዘንድሮው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከባለፉት ዓመታት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

አርሶ አደሩ የበጋ መስኖ ስንዴን በኩታ ገጠም እና በመስኖ በማልማት ውጤታማ መሆኑን ተናግረው፤ በአጠቃላይ የገጠር ሽግግርን በማሳለጥ የአርሶ አደሩን ኑሮ ለመቀየር የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ በሪሶ ፈይሳ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አራት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማልማት 163 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሰራ ነው።


 

እስካሁን ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር የመሬት ዝግጅት መደረጉን ጠቁመው፤ ከዚህ ውስጥ  አንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን አስታውቀዋል።


 

በዘር ከተሸፈነው መሬት ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው በመካናይዜሽን እና በዘመናዊ ማሽኖች በመታገዝ መታረሱን ተናግረዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ከፍያለው አዳሬ በበኩላቸው፤ በዞኑ 590 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑን፣ 85 በመቶው በመካናይዜሽን መልማቱንና 11 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጸዋል።


 

በዞኑ ተግባራዊ መደረግ በጀመረው ዘመናዊ የእርሻ ቴክኖሎጂ በመታገዝ አርሶ አደሩ ምርታማነቱን ማሳደግ መቻሉን ጠቅሰዋል።

ከዞኑ አርሶ አደሮች መካከል ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ተሾመ ስዩም እንዳሉት፤ በኩታ ገጠም እርሻ በተሰሩ ስራዎች ምርታማነታቸው  ጨምሯል።


 

ዘመናዊ ቴክኖሎጂ መጠቀም መጀመራቸው ከራሳቸው ፍጆታ ባለፈ ትርፍ አምራች በመሆን ምርታቸውን ለገበያ ለማቅረብ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል ።


 

አርሶ አደር ጌቱ ደሳለኝ በበኩላቸው፤ በዝናብና በመስኖ በማምረት ውጤታማ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ መንግስት የተሟላ ግብዓት እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ስላቀረበላቸው ትርፍ ምርት እያመረቱ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም