ቀጥታ፡

በሁለተኛው ዙር የመዲናዋ የኮሪደር ልማት 9ኛው ፕሮጀክት የአካባቢውን ደረጃ ከፍ በሚያደርግ መልኩ እየተገነባ ነው 

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 30፣ 2018(ኢዜአ)፦በሁለተኛው ዙር የአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደር ልማት 9ኛው ፕሮጀክት ሆኖ የተጨመረው ኡራኤል ፣ አትላስ ፣ ቦሌ ብራስ እና የቦሌ መድሃኔአለም ፣ ጎላጉል እንግሊዝ ኤምባሲ ፕሮጀክቶች የአካባቢውን ደረጃ ከፍ በሚያደርግ መልኩ እየተገነቡ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡

ከንቲባ አዳነች እና የከተማው አመራሮች የኮሪደር ልማቶቹን እና የፒኮክ ወይንም ማዕከላዊ ፓርክ ፕሮጀክት የግንባታ ሂደት በመስክ ጉብኝት ገምግመዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ስድስት ኮሪደሮች እና ሁለት የወንዝ ዳርቻ ልማቶች በአጠቃላይ ስምንት ፕሮጀክቶች መጀመራቸው ይታወሳል፡፡


 

ከስምንቱ ስድስቱ ኮሪደሮች ተጠናቀው ወደ አገልግሎት የገቡ ሲሆን የከተማ አስተዳደሩ የተገነቡ የፕሮጀክት ነጥቦችን የሚያገናኙ እና ተጀማምረው የቆዩ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ በተያዘው መርህ መሰረት ኡራኤል ፣ አትላስ ፣ ቦሌ ብራስ እና የቦሌ መድሃኔአለም ፣ ጎላጉል እንግሊዝ ኤምባሲ የኮሪደር ልማት ዘጠነኛው ሆኖ ስራው እየተካሄደ ይገኛል፡፡

የኮሪደር ልማቶቹን እና የፒኮክ ወይንም ማዕከላዊ ፓርክ ፕሮጀክት የግንባታ ሂደት በመስክ ጉብኝት በተገመገመበት ወቅት ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት፤ የተጀመሩት የመንገድ ፕሮጀክቶች 11 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ ናቸው፡፡

የኮሪደር ልማት ስራው የአካባቢውን ደረጃ ከፍ በሚያደርግ መልኩ እየተገነባ እንደሆነ የገለጹት ከንቲባ አዳነች ኢትዮጵያ የምታስተናግደውን 32ኛውን የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ  ታሳቢ ባደረገ መልኩ በአደይ አበባ ስታዲየም ዙሪያም ተጨማሪ ልማቶች ይሰራሉ ብለዋል፡፡


 

ፕሮጀክቱ የከተማዋን ገጽታ የሚያሳድግ ብሎም ከኮፕ 32 ጉባኤ ጋር ተያይዞ የሚመጡ እንግዶችን በአግባቡ ለማስተናገድ የሚረዳ በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ ለስኬቱ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባውም ነው ከንቲባ አዳነች የገለጹት፡፡

ከኡራኤል ፣ አትላስ ፣ ቦሌ ብራስ ኮሪደር የመንገድ ስራ አፈጻጸም ከ60 በመቶ በላይ ሲሆን ከቦሌ መድሃኔአለም ፣ ጎላጉል እንግሊዝ ኤምባሲ ያለው ደግሞ 35 በመቶ ገደማ መሆኑን የተናገሩት የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሙዲን ረሻድ፤ ፕሮጀክቱን በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የፒኮክ ወይንም ማዕከላዊ ፓርክ እና የወንዝ ዳርቻ ልማት የፕሮጀክት አፈጻጸም በመስክ ጉብኝቱ የተገመገመ ሌላው ግንባታ ሲሆን ፓርኩ አለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ተመልሶ እየተገነባ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል፡፡


 

በአዲስ መልክ እየተገነባ የሚገኘው የፒኮክ ወይንም ማዕከላዊ ፓርክ መካነ እንስሳት፣ የውሃ ላይ መዝናኛ ስፍራዎች፣ የሰርግ አዳራሾች፣ የገበያ ማዕከላት፣ ባህላዊ እና ዘመናዊ የምግብ አዳራሾች፣ መንገዶች የወንዝ ዳርቻ መናፈሻዎች፣ የኢትዮጵያውያንን የአኗኗር ስርዓት የሚያሳዩ ኪነ ህንጻዎች ፣ የልጆች መጫዎቻዎች እና ሌሎችም በርካታ መሰረተ ልማቶች ተሟልተውለት ነው እየተገነባ የሚገኘው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም