ቀጥታ፡

ቀኑ በህዝቦች መካከል አብሮነትን እና አንድነትን ለማጠናከር የተጀመረውን ጥረት በሚያጎለብት መልኩ ተከብሯል 

ሆሳዕና ፤ ሕዳር 30/2018(ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተከበረው 20ኛው የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በህዝቦች መካከል አብሮነትን እና አንድነትን ለማጠናከር የተጀመረውን ጥረት በሚያጎለብት መልኩ መከበሩን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለፁ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ የበዓሉን በስኬት መጠናቀቅ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፣ በዓሉ በትብብር መስራት ተጨባጭ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ተሞክሮ የተወሰደበት ነው ብለዋል፡፡

በዓሉ በስኬት እንዲጠናቀቅ የክልሉ መንግስት ህብረተሰቡን በማስተባበር ከተሞችን ውብና ፅዱ ከማድረግ ጀምሮ በዓሉን ለማድመቅ የሚሆኑ የመሰረተ ልማቶችን በአጭር ጊዜ ማከናወን መቻሉን ተናግረዋል።

የክልሉ ህዝብም እንግዶችን ተቀብሎ በማስተናገድ ያሳየው ተሳትፎ የጋራ ትርክት ለመገንባት የተጀመረውን ጥረት ለማጠናከር ትልቅ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

ከሁሉም በላይ በዓሉ በህዝቦች መካከል አብሮነትን እና አንድነትን ለማጠናከር የተጀመረውን ጥረት በሚያጎለብት መልኩ መከበሩንም አክለዋል።

የመንግሥትን አቅምና የማህበረሰቡን ተሳትፎ በማቀናጀት መስራት ከተቻለ ለስኬት መብቃት እንደሚቻል በተጨባጭ የታየበት መሆኑን አስረድተዋል።

በዓሉ በስኬታማነት እንዲጠናቀቅ በተለያየ መንገድ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና ያቀረቡት ርዕሰ መስተዳደሩ በተለይም የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ጨምሮ የአጎራባች ክልሎችና የጸጥታ መዋቅር አካላት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና ይገባል ብለዋል፡፡ 

የሚዲያ አካላትም ክልሉን በማስተዋወቅ፣ የክልሉ ህዝብ እንግዶችን በመቀበል እንዲሁም የክልሉ አመራር በማስተባበር ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይም በክልሉ በሁሉም መዋቅሮች የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም