ከምንም በላይ የምንሻው ሰላምን ማፅናትና ልማትን ማረጋገጥ ነው- የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ከምንም በላይ የምንሻው ሰላምን ማፅናትና ልማትን ማረጋገጥ ነው- የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች
መቀሌ፤ ሕዳር 30/2018(ኢዜአ)፦ከምንም በላይ አሁን የምንሻው ሰላምን ማፅናትና ልማትን ማረጋገጥ ነው ሲሉ የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
የትግራይ ክልል ህዝብ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት በማግኘት የልማት ተጠቃሚ መሆንን አጥብቆ የሚመኝና ለዚህም የሚሰራ መሆኑ ይታወቃል።
በዚህም መሰረት የፌዴራል መንግስት በክልሉ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ሰፍኖ የህዝቡ የልማት ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ እየሰራ ይገኛል።
በዚህ ጥረት ውስጥ በተለይም የህዝቡ ድጋፍና ትብብር ከታከለበት የታለመውን ስኬት፣ ዘላቂ ሰላምና ተጠቃሚነትን በቀላሉ ማረጋገጥ ያስችላል።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎችም ከምንም በላይ አሁን የምንሻውን ሰላም ማፅናትና ልማትን ማረጋገጥ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል በሃውልት ክፍለ ከተማ በንግድ ዘርፍ የተሰማሩት ሀጂ ሰዒድ ሁሴን፤ የሰላምና የልማት ዋነኛ ባለቤትና ተጠቃሚውም ህዝብ በመሆኑ በዚሁ ልክ ሁላችንም መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
በትግራይ ክልል ከዚህ በፊት በነበሩ ግጭቶች ህዝቡ የችግሩ ገፈት ቀማሽ በመሆን ብዙ ዋጋ ስለመክፈሉ አስታውሰው አሁን ላይ ግን ሁሉም ሰላምና ልማትን ይሻል፤ ለዚህም ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
ያም ሆኖ ከሁሉም በፊት ሰላምን ካላስቀደምን በሌሎች የሀገራችን ክፍሎች እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን ወደ ክልሉ በማምጣት ለመተግበር እንቸገራለን ብለዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የሰሜን ክፍለ ከተማ ነዋሪው አስር አለቃ ተካ ዘገየ፤ የሰላም እጦት የሚያመጣው ዘርፈ ብዙ ችግር ምን እንደሚመስል የታየ መሆኑን አስታውሰው አሁን የመጣውን ሰላምና የተጀመረውን ልማት ማስቀጠል የሁላችንም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ሰላማችንን አስጠብቀንና ልማታችንን አረጋግጠን መዝለቅ ለማንም የማይተው የጋራ ሃላፊነታችን ነው ያሉት ደግሞ በከተማዋ የሃይደር ክፍለ ከተማ ነዋሪው አቶ አረጋዊ ጉላል ናቸው።
የህዝብ ጠንካራ ተሳትፎ የታከለበት የሰላምና የልማት ስራ በውጤታማነት የሚዘልቅ መሆኑን አንስተው ለዚህም የላቀ ሚናችንን እንወጣለን ሲሉም አረጋግጠዋል።