ቀጥታ፡

ከተላላፊ በሽታዎች ለመጠበቅ የጥንቃቄ መልዕክቶችን ተግባራዊ ማድረግ ይገባል

ሕዳር 30/2018(ኢዜአ)፦ ህብረተሰቡ የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን የጥንቃቄ መልዕክቶች ተግባራዊ በማድረግ ራሱን ከተላላፊ በሽታዎች መጠበቅ እንዳለበት ተመላከተ። 

የሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር ጤና ጽህፈት ቤት ከኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር በተላላፊ በሽታዎቸ ዙሪያ ያዘጋጀው መድረክ በሻሸመኔ ከተማ ተካሄዷል።

የክልሉ ጤና ቢሮ የህብረተሰብ ድንገተኛ ጤና ቁጥጥርና ምርምር ዳይሬክተር ገመቹ ሹሜ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በክልሉ ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል ማህበረሰቡን ባሳተፈ መልኩ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል።


 

ፖሊዮና ሌሎች መሰል በሽታዎችን ከሀገር ለማጥፋት በተያዘው አቅጣጫ እንደ ክልል በዘመቻ ህጻናት ክትባት እንዲወስዱ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሱልጣን ሁሴን በበኩላቸው፤ በተላላፊ በሽታዎች ዙሪያ የማህበረሰቡን ግንዛቤ የሚያሳድጉ መርሀ ግብሮችን በማዘጋጀት የማስተማር ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።


 

በክትባት ለመከላከል የሚቻሉ እንደ ኩፍኝና ፖሊዮን የመሳሰሉ በሽታዎች አስቀድሞ የመከላከል ስራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የአዳማ ጤና ጽህፈት ቤትን በመወከል በመድረኩ የተሳተፉት ሲስተር ሰሚራ መሀመድ እንዳሉት፤ በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰቱ ተላላፊ በሽታዎችን አስቀድሞ ለመግታት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል።


 

በበሽታዎቹ ዙሪያ የሃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች፣ ሃደ ሲንቄዎችና መምህራንን በማሳተፍ ከትምህርት ቤቶችና በእምነት ተቋማት ጋር በመተባበር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በመርሐግብሩ ላይ የኦሮሚያ ክልል የጤናው ዘርፍ አመራሮች፣ የሻሸመኔ ከተማ የጤና ባለሙያዎች፣ የአዳማና ሌሎች ከተሞች ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን በመድረኩም በተላላፊ በሽታዎች ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም