ያገኘነውን ዕውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ አካባቢያችንን ለማልማት ቁርጠኞች ነን - ኢዜአ አማርኛ
ያገኘነውን ዕውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ አካባቢያችንን ለማልማት ቁርጠኞች ነን
ዲላ/ ወላይታ ሶዶ ፤ ሕዳር 30/2018(ኢዜአ)፦ በስልጠናው ያገኙትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ አካባቢያቸውን ለማልማት ቁርጠኞች መሆናቸውን የጌዴኦ ዞንና የዲላ ከተማ ሰልጣኝ አመራሮች ገለጹ።
በጌዴኦ ዞንና በዲላ ከተማ አስተዳደር "በመደመር መንግስት እይታ፣ የዘርፎች እመርታ" በሚል መሪ ሃሳብ ለ3ኛ ዙር ለመካከለኛ አመራሮች የተሰጠው ስልጠና ተጠናቋል።
አመራሮቹ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በስልጠና ያገኙትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ ለአካባቢያቸው እድገት የበኩላቸውን ይወጣሉ፡፡
ስልጠናው በብዝሃ ኢኮኖሚ ልማት ያላቸውን ግንዛቤ ከማሳደግ ባለፈ ዞኑ በግብርናና በቱሪዝም ልማት ያለውን አቅም አውጥቶ ለመጠቀም በርብርብ ለመስራት ቁርጠኝነታቸውን አረጋግጠዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡ ሰልጣኝ አመራሮች መካከል ወይዘሮ ውዴ አብርሃም፣ ስልጠናው በተለይም በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በከተማ መሠረተ ልማትና በቱሪዝም ዘርፍ ያላቸውን ግንዛቤ ያሳደገ መሆኑን ተናግረዋል።
በተግባር በተደገፈ ስልጠና ያገኙትን እውቀት ወደ መሬት በማውረድ ለአካባቢያቸው ልማትና ለብልፅግና ጉዞ መፋጠን የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
ስልጠናው ያሉ ሀብቶችን በማስተባበር እንዴት ወደ ውጤት መቀየር እንደሚቻል አቅም ያገኘንበት ነው ያሉት ደግሞ አቶ ተክሉ አራርሶ ናቸው።
በመፍጠን እና መፍጠር እሳቤ ለዞኑ እድገት እንደሚሰሩ ገልጸው፣ በስልጠናው መነሻ ፀጋዎችን ለይተው በመስራት ለአካባቢያቸው እድገት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ሌላኛዋ ሰልጣኝ ወይዘሮ ራሄል ግርማ በበኩላቸው፤ ስልጠናው የብልፅግና ፓርቲ መዳረሻን በበቂ ሁኔታ የዳሰሰና ግንዛቤን ያስጨበጠ ነው ብለዋል።
ይህም የፓርቲውን እሳቤዎች ተገንዝበን ወደታች በማውረድ ለተጀመረው የብልፅግና ጉዞ መፋጠን በትኩረት ለመስራት አቅም ይሆነናል ብለዋል።
የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር)፤ አመራሩ የወሰደውን ስልጠና ወደ ተግባር በመለወጥ በየዘርፉ እመርታዊ ውጤትን ለማስመዝገብ በቁርጠኝነት መስራት አለበት ብለዋል።
በተለይም በዞኑ በቡናና እንሰት ልማት፣ በገቢ አሰባሰብ እንዲሁም የቁጠባ ባህልን በማዳበር ረገድ የተጀመሩ ስራዎችን በማጠናከር ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የሚደረገውን ጥረት ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።
የዞኑን እምቅ ሀብቶችና የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማስተዋወቅ የቱሪዝም ዘርፍ እመርታን ማረጋገጥ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በተመሳሳይ በወላይታ ሶዶ በተሰጠው ስልጠና ማጠቃለያ ላይ የተገኙት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ሳሙኤል ተሰማ (ረዳት ፕሮፌሰር) በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በከተማ ልማት፣ በኢንዱስትሪ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ተለይቶ የተሰጠው ስልጠና የአመራሩን አቅምና ተነሳሽነት ያሳደገ ነው ብለዋል።
በዞኑ በርካታ የመልማትና የማደግ አቅም እንዳለ ጠቅሰው፣ የሜካናይዜሽን እርሻና የግብርና ቴክኖሎጂን በመተግበር የምርት መጠንን ለማሳደግና ህዝቡን ከተረጂነት ለማላቀቅ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በሌማት ትሩፋት ዘርፍም የወተት፣ የማር፣ የሥጋ፣ የአሣ፣ የእንቁላል፣ የአትክልትና ፍራፍሬ መንደር በመፍጠር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመረው ስራ ይጠናከራል ብለዋል፡፡
ከወላይታ ሶዶ ሰልጣኝ አመራሮች መካከል አቶ ሀብታሙ ሙላቱ እንደገለጹት፤ ስልጠናው የውስጥ ፀጋዎችንና አቅሞችን ለይቶ ወደ ውጤት በመቀየር የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተነሳሽነትን የፈጠረ ነው።
ወይዘሮ ሰላማዊት መኮንን በበኩላቸው ፤ስልጠናው በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በከተማ ልማት እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ያለንን አቅም ተረድተን የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ አቅም ያገኘንበት ነው ብለዋል።
በዞኑ ያሉትን የተፈጥሮ ጸጋዎች ወደ ልማት መቀየር ከተቻለ ህዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል ገልጸው፣ በስልጠና ያገኙትን አቅም በመተግበር የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።