የሊጉ መሪ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ሽንፈቱን አስተናገደ - ኢዜአ አማርኛ
የሊጉ መሪ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ሽንፈቱን አስተናገደ
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 30/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 11ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ቦሌ ክፍለ ከተማ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2 ለ 1 አሸንፏል።
በአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ዳሳሽ ሰውአገኝ እና ሚሊዮን ጋይም የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
ዳግማዊት ሰለሞን ለኢትዮ ኤሌክትሪክ ብቸኛውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፋለች።
የሊጉ መሪ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያለመሸነፍ ጉዞ 11ኛ ሳምንት ላይ ተገቷል። ቡድኑ 30 ነጥብ ላይ ረግቷል።
በአንጻሩ በሊጉ አምስተኛ ድሉን ያስመዘገበው ቦሌ ክፍለ ከተማ በ19 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል።
የኢትዮ ኤሌክትሪኳ አጥቂ ዳግማዊት ሰለሞን በውድድር ዓመቱ ያስቆጠረቻቸውን ግቦች ወደ 17 ከፍ በማድረግ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት መሪነቷን አጠናክራለች።
ዛሬ በተደረገው ሌላኛው ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድሬዳዋ ከተማን 1 ለ 0 አሸንፏል።
ጨዋታዎቹን ተከትሎ የ11ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ተጠናቋል።
የ12ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከታህሳስ 3 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ እንደሚካሄዱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።