በከተማዋ ሰላምን በማፅናት የተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በከተማዋ ሰላምን በማፅናት የተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ
ደሴ ፤ ሕዳር 30/2018(ኢዜአ)፦ በደሴ ከተማ ሰላምን በማፅናት በተለያዩ ዘርፎች የተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የከተማዋ አስተዳደር አስታወቀ።
የከተማዋ ምክትል ከንቲባ አቶ ሽመልስ ጌታቸው በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ በከተማው በሚመነጨው ኢኮኖሚ ልክ ገቢ በመሰብሰብ የሕብረተሰቡን የልማት ጥያቄ በየደረጃው ለመመለስ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል።
በተጨማሪም በገበያ ማረጋጋት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በከተማ ግብርና፣ በኢንቨስትመንትና በሌሎችም ዘርፎች አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህም ባለፉት አራት ወራት አንድ ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን፣ ከ10 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ እድል መፈጠሩን እና 310 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ የማልማት ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል።
እንዲሁም ከተማ አስተዳደሩ በመደበው ከፍተኛ ገንዘብ ምርት በማቅረብ ገበያውን ዋጋ ማረጋጋት መቻሉን ጠቁመው፤ ህገ ወጥ ንግድን በመከላከል ጤናማ የንግድ ስርዓትን መፍጠር መቻሉንም አንስተዋል።
ካለፈው ዓመት ጀምሮ ከ2 ሺህ በላይ ንግድ ፍቃድ ሳይኖራቸው ይሰሩ የነበሩ ነጋዴዎችን በመምከርና በማስተማር ወደ ህጋዊ ንግድ ስርዓት እንዲገቡ መደረጉንም አንስተዋል።
በከተማው በኢኮኖሚው ዘርፍ የተገኘውን አበረታች ውጤት የበለጠ አጠናክሮ ለማስቀጠል እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
በከተማ ግብርናና በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በውስን ቦታ ላይ ምርታማነትን ለማሳደግና ህብረተሰቡ በምግብ ራሱን እንዲችል ተገቢው ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
እንደ ምክትል ከንቲባው ገለጻ ኢንዱስትሪዎችን በመደገፍና መሰረተ ልማት በማሟላት ተኪ ምርት እንዲያመርቱ ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር ባለፈ ያመረቱትን ምርት ለውጪ ገበያ ጭምር እንዲያቀርቡ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የመሰረተ ልማት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
በቀጣይም ከህብረተሰቡ ጋር እየተከናወነ ያለውን የከተማውን ሰላም የመጠበቅ ተግባራት በማጠናከር የተጀመሩ የልማት ስራዎች እንደሚፋጠኑም አረጋግጠዋል።