ቀጥታ፡

በሕብረተሰቡና በጸጥታ መዋቅሩ የተቀናጀ ርብርብ በጎንደር አስተማማኝ ሰላም ማስፈን ተችሏል

ጎንደር፤ ሕዳር 30/2018(ኢዜአ)፡- በጎንደር ከተማ በሕብረተሰቡና በጸጥታ መዋቅሩ የተቀናጀ ርብርብ እና ድጋፍ  አስተማማኝ ሰላም ማስፈን መቻሉን የከተማ አስተዳደሩ  ሰላምና ጸጥታ መምሪያ አስታወቀ፡፡

በከተማ አስተማማኝ ሰላም መስፈኑን ተከትሎ በምሽት  የሰውና የተሸከርካሪ እንቅስቃሴ ላይ ተጥሎ የነበረው ገደብ ሙሉ በሙሉ መነሳቱን መምሪያው ገልጿል።

የከተማ አስተዳደሩ ሰላምና ጸጥታ መምሪያ  ሃላፊ አቶ አለልኝ አለም በሰጡት መግለጫ ፤ በሕብረተሰቡና በጸጥታ መዋቅሩ የተቀናጀ ርብርብና ድጋፍ አሁን ላይ የከተማው ሰላም አስተማማኝ ደረጃ ላይ መድረሱን አስታውቀዋል፡፡

በከተማው እየተከናወኑ የሚገኙ  የኮሪደር ልማት ስራዎችና ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ምሸት ጭምር እየተሰሩ ያሉት  ሰላማዊ ድባብ በመፈጠሩ እንደሆነ አንስተዋል። 

ሰላሙን በዘላቂነት ከማረጋገጥ ጎን ለጎን በከተማው የሰውና የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ባልተገደበ መንገድ 24 ሰዓት እንዲከናወን ለማስቻልም የምሽት የሰዓት ገደብ እንዲነሳ በከተማ አስተዳደሩ መወሰኑን ይፋ አድርገዋል፡፡

በቀጣይ ጥር ወር በሚከበረው የጥምቀት በዓል እንግዶችና ቱሪስቶች ባልተገደበ እንቅስቃሴ በበዓሉ ላይ መታደም እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም አረጋግጠዋል፡፡

ሕብረተሰቡ በብሎክ ተደራጅቶ እያደረገ ያለውን የሰላም ማስከበር ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበው፤  የጸጥታ መዋቅሩም ተልዕኮውን በሙሉ ሃላፊነት እንደሚወጣም አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም