ቀጥታ፡

የስንዴ ልማት ኢኒሼቲቭ የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያሳደገ ነው   

መቱ፤ ሕዳር 30/2018(ኢዜአ)፦ የኦሮሚያ ክልል  የስንዴ ልማት ኢኒሼቲቭ  የአርሶ አደሩን  ኢኮኖሚያዊ አቅም እያሳደገው መምጣቱን በብልጽግና ፓርቲ የክልሉ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ነመራ ቡሊ ተናገሩ።

የክልሉ መንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በተገኙበት በኢሉአባቦር ዞን ቡሬ ወረዳ  የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በይፋ ተጀምሯል።

በብልጽግና ፓርቲ የክልሉ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ነመራ ቡሊ፣ የስንዴ ልማት በግብርናው ዘርፍ የምግብ ዋስትናና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ የሀገር ሉዓላዊነት የማስቀጠል ጉዳይ ነው ብለዋል።

በመሆኑም በክልሉ ጊዜንና የውሃ ሀብትን በአግባቡ በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።


 

የክልሉ መንግስትም አርሶ አደሩ የዝናብ ወቅትን ብቻ ጠብቆ ከማምረት ወጥቶ በአመት ሁለቴና ከዚያ በላይ በማምረት ውጤታማ የሚሆንበትን የግብአትና የቴክኖሎጂ ድጋፍ በተከታታይ እያቀረበ መሆኑን ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ ፤በክልሉ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ  ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል።

ከታቀደው አጠቃላይ መሬት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ሔክታር በላይ የማሳ ዝግጅት መጠናቀቁንና ከዚህም 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ሔክታሩ በዘር መሸፈኑንም ገልጸዋል።


 

የበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱም ምርትና  ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ  በእጅጉ ያግዛል ብለዋል።

በቀሪ የበጋ ወራትም ጊዜንና የውሃ ሀብትን በአግባቡ በመጠቀም የመስኖ ልማት እቅዱን ለማሳካት በትኩረት እንደሚሰራ ጠቅሰው የግብአት አቅርቦትና ሙያዊ ድጋፍም ይጠናከራል ነው ያሉት።

የበጋ መስኖ የስንዴ ልማቱ ባለፉት ዓመታት በንቅናቄ ሲካሄድ የነበረውን ተግባር አሁን ላይ አርሶ አደሩ በመደበኛነት መቀጠሉንም አውስተዋል።

በኢሉአባቦር ዞንም በበጋው ወቅት 120 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ ስንዴ እየለማ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኢሉአባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ ናቸው።

በስራውም ምርታማነትን ለመጨመር የሚያስችል የግብአት አቅርቦት ተደራሽ መደረጉን ገልጸዋል። 


 

በቡሬ ወረዳ በበጋ ስንዴ ልማት ከተሰማሩ አርሶ አደሮች መካከል የቶሊ ጬካ ቀበሌ ነዋሪው አቶ መሐመድ አስረስ እና አቶ ረታ ከበደ  እንዳሉት፤  በማህበር በመደራጀት በ35 ሔክታር መሬት ላይ የበጋ መስኖ ስንዴ እያለሙ ይገኛሉ።

በልማቱ ውጤታማ ለመሆን በጋራ በመስራት ገንዘባቸውንና ጉልበታቸውን ማቀናጀታቸውን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም