ቀጥታ፡

በአማራ ክልል 62 ሺህ 977 ሄክታር መሬት ላይ የደረሰ የሩዝ ሰብል ተሰበሰበ

ባሕር ዳር ፤ ሕዳር 30/2018 (ኢዜአ) ፡- በአማራ ክልል በመኸር ወቅቱ  በሩዝ ሰብል ከለማው መሬት ውስጥ 62 ሺህ 977 ሄክታር  ላይ የደረሰውን ምርት መሰብሰብ መቻሉን  የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የድህረ ምርት ቴክኖሎጂ ባለሙያ አቶ ምትኩ መላኩ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ ለሩዝ ሰብል ልማት ተስማሚ በሆኑ አካባቢዎች ልማቱን በማስፋት ከውጭ የሚገባውን የሩዝ ምርት ለማስቀረት ትኩረት ተሰጥቶ  እየተሰራ ነው።

ለዚህም በክልሉ በ2017/2018 የምርት ዘመን ከ208 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ  የሩዝ ሰብል መልማቱን ተናግረዋል።

ከለማው መሬት እስካሁን 62 ሺህ 977 ሄክታር መሬት ላይ የደረሰ የሩዝ ሰብል የምርት ብክነትን መከላከል በሚያስችል አግባብ መሰብሰብ መቻሉን አስታውቀዋል።


 

ቀሪው በሩዝ ሰብል የለማው መሬት በቀጣይ ተሰብስቦ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ከ12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።  

ቀደም ሲል በደቡብና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች ብቻ ይመረት የነበረውን የሩዝ ሰብል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሉ ለሩዝ ሰብል ልማት ተስማሚ በሆኑ ዞኖች ልማቱን በማስፋፋት አርሶ አደሩ ተጠቃሚ  በመሆን ላይ እንደሚገኝ  አመልክተዋል።

በደቡብ ጎንደር ዞን የፎራ ወረዳ አርሶ አደር መኳንንት ዘሩ በሰጡት አስተያየት፤  ምርታማ በሆኑት "ሰላም፣ ሻጋና ኤክስ ጀግና "  በተሰኙ የሩዝ ሰብሎች ካለሙት አንድ ሄክታር ከሩብ መሬት እስካሁን ግማሽ ያህሉን መሰብሰብ እንደቻሉ ተናግረዋል።

በዚህም በአጠቃላይ ከ85 ኩንታል በላይ ምርት አገኛለሁ ብዬ አጠብቃለሁ ብለዋል።

የሩዝ ሰብል የምግብ ፍጆታቸውን እንዲሸፍኑ ከማድረግ ባለፈ ምርቱን ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንዳስቻላቸው የገለጹት ደግሞ  የዚሁ ወረዳ  አርሶ አደር መልኬ መለሰ ናቸው።

በዘንድሮው የመኸር ወቅትም ምርታማ በሆኑ የሩዝ ሰብል ዝርያዎች ያለሙትን አንድ ሄክታር ተኩል መሬት ምርቱን እየሰበሰቡ መሆኑን ተናግረዋል።

የምርት አያያዙ የተሻለ በመሆኑ ከ90 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚያገኙ  አንስተዋል።

በዞኑ የሊቦከምከም ወረዳ አርሶ አደር መላኩ ሰጠኝ በበኩላቸው፤ በመኸሩ ወቅት የተሻለ ግብዓት ተጠቅመው ያለሙት የሩዝ ሰብል የምርት አያያዙ የተሻለ በመሆኑ ጥሩ ምርት አገኛለሁ ብለው እንደሚጠብቁ ገልጸዋል። 

ከግብርና ቢሮው የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በአማራ ክልል በ2016/2017 የምርት ዘመን በሩዝ ሰብል ከለማው 150 ሺህ 762 ሄክታር መሬት ከ8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተገኝቷል  ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም