ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የኒውክሌር ልማት ከአየር ንብረት ጋር የተጣጣመ ጠንካራ ኢኮኖሚ ሥርዓት የመገንባት ርዕይን ያነገበ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 30/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሰላማዊ የኒውክሌር ልማት ከአየር ንብረት ጋር የተጣጣመ በአስተማማኝ የኃይል አቅርቦት የተመሠረተ ጠንካራ የኢኮኖሚ ሥርዓት የመገንባት ርዕይን ያነገበ መሆኑን የኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ኮሚሽነር ሳንዶካን ደበበ ገለጹ።

የመጀመሪያው ብሔራዊ የኒውክሌር ኃይል መርሃ ግብር ሚናና ኃላፊነት የተቋም ትግበራ አውደ ጥናት የምክክር መድረክ መካሄድ ጀምሯል።

ከዛሬ ኅዳር 30 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ቀናት በሚቆየው የአውደ ጥናት መድረክ የኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ኮሚሽነር ሳንዶካን ደበበ፣ የዓለም አቀፍ አቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሚካኤል ቹዳኮቭና የባለድርሻ ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።


 

የኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ኮሚሽነር ሳንዶካን ደበበ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ አስተማማኝ፣ ተዓማኒነትና ሰላማዊ የኒውክሌር መርሃ ግብር ለመገንባት ቁልፍ እርምጃ ጀምራለች።

የኢትዮጵያ ሰላማዊ የኒውክሌር ልማት ከአየር ንብረት ጋር የተጣጣመ ጠንካራ የኢኮኖሚ ሥርዓት የሚገነባ አስተማማኝ የኃይል አቅርበት መፍጠርን ርዕይ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የኒውክሌር ኃይል ልማት ሥራም ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትና የህዝብ ቁጥርን ታሳቢ በማድረግ በኃላፊነት፣ ግልጽነትና ከዓለም አቀፍ የደኅንነት ጥበቃና ደረጃዎች ጋር ተጣጥሞ የሚተገበር መሆኑን ተናግረዋል።

በዓለም አቀፍ አቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ እና በባለድርሻ አካላት ጋር በሚደረግ ጠንካራ ትብብር የተመሠረተ አጋርነት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ሰላማዊ የኒውክሌር ልማት የጤና፣ ግብርና፣ ኢንዱስትሪ ሳይንስና ምርምር ዘርፎችን ተወዳዳሪነት የሚያልቅ ብሔራዊ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

የዓለም አቀፍ አቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሚካኤል ቹዳኮቭ፤ የኢትዮጵያ የኒውክሌር ልማት ለአፍሪካና ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ወሳኝ ወደ ፊት የመራመድ ምልክት እንደሆነም ገልጸዋል።


 

ይህም የኢትዮጵያን የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ልማትና ብልጽግና የሚደግፍ ንጹህ፣ አስተማማኝና ዘላቂ የኃይል ደኅንነትን ለማስጠበቅ ስትራቴጂያዊ ምልክት ተደርጎ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የኒውክሌር ልማት ርዕይም ከህዝቧ የዕድገት ምኞት ባለፈ ከአፍሪካ የመለወጥ ህልም ጋር የተጣጣመ መሆኑን አስታውቀዋል።

በርካታ ሀገራትም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተጣጣመ ዕድገትን ለማስቀጠል የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎትና ደኅንነትን የሚያጠናክር የኒውክሌር ኃይል መርሃ ግብሮችን እየመረመሩ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያን የኒውክሌር ልማት መርሃ ግብር ደህንነት፣ አስተማማኝነትና ዘላቂነትም ከሀገራዊ ራዕይ ጋር የተጣጣመ እንዲሆን የሚያደርጉትን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

በዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ የቴክኒክ ትብብር መምሪያ የአፍሪካ ጉዳዮች ክፍል ተጠባባቂ ዳይሬክተር ጋሻው ገበየሁ፤ ኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ልማት መርሃ ግብርን ለመጀመር የወሰደችው ውሳኔ ደፋርና ሩቅ አሳቢነት ያመላከተ ነው ብለዋል።


 

የሀገርን ዕድገት በአስተማማኝና ደኅንነቱ በተጠበቀ የኃይል አቅርቦት ልማትን ማሳለጥ እንደሚያስፈልግ የሚያስገነዝብ መሆኑንም ገልጸዋል።

ለቀጣዩ ትውልድ ጠንካራና የበለጸገች ሀገር ማውረስ የሚያስችል ቁርጠኝነትን እንደሚያሳይም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ልማት መሻት በጤና፣ በትምህርት፣ በኢንዱስትሪ ዕድገትና በአካባቢ ጥበቃ ከማሳለጥ ባሻገር የኒውክሌር ባለሙያዎች፣ መሐንዲሶች፣ ተቆጣጣሪዎች፣ ተመራማሪዎችና የፖሊሲ አውጪ ትውልድ የሚቀርፅ ዕድል ነው ብለዋል።

በቀጣይም በቴክኒክ ትብብር፣ በሰው ሃብት ልማት፣ ዓለም አቀፍ የማዕቀፍ ትግበራ እና ሌሎች መስኮች በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም