ቀጥታ፡

ሆስፒታሉ በቅርቡ የጀመረው የካንሰር የጨረር ሕክምና ተገልጋዮችን ከእንግልት ታድጓል

ጎንደር ፤ ሕዳር 30/2018(ኢዜአ)፦ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በቅርቡ የጀመረው የካንሰር የጨረር ሕክምና አገልግሎት ከእንግልትና ከውጣ ውረድ ታድጎናል ሲሉ ታካሚዎች ተናገሩ፡፡

ሆስፒታሉ በቅርቡ በጀመረው የጨረር ሕክምና አገልግሎት ከ100 በላይ የካንሰር ሕሙማን አገልግሎት ማግኘት እንደቻሉም አስታውቋል፡፡

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ ሕሙማን መካከል ወይዘሮ ዳሳሽ ጠጋው፤ ለረጅም ዓመታት በማህጸን በር ካንሰር ታመው በጨረር ሕክምና እጦት ከባድ የሕመም ጊዜ ማሳለፋቸውን ተናግረዋል፡፡

ወደ አዲስ አበባ ሄዶ ለመታከም የኢኮኖሚ አቅም ስለሌላቸው ለብዙ ጊዜ ከሕመማቸው ጋር እንደቆዩ አስታውሰው፤ ሆስፒታሉ በቅርቡ በጀመረው የጨረር ሕክምና አገልግሎት ተጠቃሚ በመሆን ከበሽታው መዳናቸውን ተናግረዋል፡፡ 

ወይዘሮ አጥቢያነሽ ገብሩ የተባሉ ሌላኛዋ የካንሰር ታካሚ በበኩላቸው ፤ በጡት ካንሰር ታመው ለረጅም ጊዜ ሕክምና ሲከታተሉ  መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡


 

ሆስፒታሉ በጀመረው የጨረር ሕክምና ተጠቃሚ ከሆኑ በኋላ ከበሽታቸው ሙሉ በሙሉ መዳናቸውን በሀኪሞቻቸው ማረጋገጫ እንደተሰጣቸውም ተናግረዋል፡፡

ላለፉት 10 ዓመታት በሆስፒታሉ ከጨረር ሕክምና ውጪ ለካንሰር ሕሙማን የሕክምና አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን የተናገሩት ደግሞ የሆስፒታሉ የካንሰር ሕክምናና ምርምር ማዕከል ሃላፊ ዶክተር ኤፍሬም ታፈሰ ናቸው። 

ሆስፒታሉ ሕክምናውን መስጠት የጀመረው በስምንት አልጋዎችና በሁለት ሀኪሞች እንደነበር አስታውሰው በአሁኑ ወቅት በ50 ሀኪሞችና በ60 አልጋዎች ለህጻናትና አዋቂዎች የካንሰር ህክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።


 

ሆስፒታሉ በቅርቡ በጀመረው የካንሰር ጨረር ሕክምና ተመዝግበው አገልግሎት ለማግኘት ወረፋ ከሚጠባበቁ 230 የካንሰር ሕሙማን መካከል ከ100 በላይ የሚሆኑት አገልግሎቱን ማግኘታቸውንም ጠቁመዋል፡፡ 

ቀደም ሲል አቅም ያላቸው ታካሚዎች ብቻ አዲስ አበባ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሄደው ይታከሙ እንደነበር ዶክተር ኤፍሬም ገልጸው፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ህክምናውን መስጠት መጀመሩ ለብዙዎች እፎይታ ሰጥቷል ብለዋል። 

መንግስት ሕክምናውን ተደራሽ ለማድረግ በሰጠው ልዩ ትኩረትም በአሁኑ ወቅት በ800 ሚሊዮን ብር ወጪ 194 አልጋዎች ያሉት የካንሰር ሕክምና መስጫ ማዕከል ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑንና ግንባታውም 70 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል፡፡

እንደ ዶክተር ኤፍሬም ገለጻ፣ ማዕከሉ በኬሞ ቴራፒና በጨረር ሕክምና የታገዘ የማህጸን በር ጫፍ ካንሰርና የጡት ካንሰር የምርመራና የህክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

በቀጣይም የደም ካንሰር ሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ማቀዱን ነው የተናገሩት።

በአሁኑ ወቅት የካንሰር ስርጭትና የታማሚዎች ቁጥር  እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው፣ አጋላጭ ከሆኑ ምክንያች መካከል አልኮልና ሲጃራን ጨምሮ የተዛባ የአመጋገብ ስርአት እንደሚጠቀሱ አመልክተዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በዓመት 400 ሺህ ለሚጠጉ ተመላላሽና ተኝቶ ታካሚዎች የሕክምና አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡     

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም