የምርምር ማዕከሉ የሩዝ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የምርምር ማዕከሉ የሩዝ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰራ ነው
ጂንካ፤ህዳር 30/2018 (ኢዜአ)፡-የጂንካ ግብርና ምርምር ማዕከል የተሻሻሉ የሩዝ ዝርያዎችን በማላመድ የሩዝ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት የሩዝ ልማት ዕድገትን አስመልክተው ሲናገሩ በኢትዮጵያ ሩዝ በፎገራ አካባቢ ይመረት እንደነበረና ምርቱም ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል የዘለለ እንዳልሆነ ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ማብራሪያቸው በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከ63 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ሩዝ እየተመረተ መሆኑን መግለፃቸውም የሚታወስ ነው።
በአሁኑ ወቅት ከዚህ ቀደም ምንም ዓይነት ምርት በማይካሄድባቸው እንደ ሶማሌ ክልል ባሉ አካባቢዎች ሩዝ በስፋት እየለማ ይገኛል። መንግስት ለልማቱ ትኩረት በመስጠቱም በቅርብ ዓመታት ውስጥ ምርቱ ከተጠቀሰውም እንደሚልቅ ማሳያዎቹ በርካታ ናቸው።
የጂንካ ግብርና ምርምር ማዕከልም የተሻሻሉ የሩዝ ዝርያዎችን በማላመድ የሩዝ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
የምርምር ማዕከሉ ቀደም ሲል በሩዝ ምርት በማይታወቁት በደቡብ ኦሞና በአሪ ዞኖች የተሻሻሉ አዳዲስ የሩዝ ዝርያዎችን በማላመድ ለአርሶና አርብቶ አደሩ እያስተዋወቀ ይገኛል።
የምርምር ማዕከሉ ዳይሬክተር ተክሌ ዮሴፍ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለፁት አርሶ አደሩ ከተለመደ የአመራረት ዘይቤ ተላቆ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ግብርናውን እንዲያዘምን በሳይንሳዊ ጥናት የታገዘ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
አካባቢው ለሩዝ ምርት ተስማሚ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፥ በቀጣይም ሩዝ እንደ ሌሎች ሰብሎች በቋሚነት ማልማት እንዲቻል ማዕከሉ የዘር ብዜት ስራውን በስፋት እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በአካባቢው ያለውን ፀጋ እና ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ከውጭ የሚገባውን የሩዝ ምርት ለመተካት እየተሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል ።
በምርምር ማዕከሉ የሰብል ተመራማሪ አወቀ ታደሰ በበኩላቸው ማዕከሉ በ10 ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ የሩዝ ዝርያዎችን ሲያላምድ መቆየቱን ጠቁመዋል ።
ማዕከሉ ካላመዳቸው የሩዝ ዝርያዎች "ዕድገት'' ፣ ''ፎገራ-1" እና ''ፓዌ -2" የተሰኙ የሩዝ ዝርያዎች ለአካባቢው ስነ-ምህዳር ተስማሚና በሄክታር እስከ 78 ኩንታል ምርት መስጠት የሚችሉ በመሆናቸው ተመራጭ አድርጓቸዋል ብለዋል።
በተለይ እነዚህ የሩዝ ዝርያዎች በአጭር ጊዜ ሊደርሱ የሚችሉ እና በበሽታና በተባይ የማይጠቁ በመሆናቸው ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል ።
እስካሁን በደቡብ ኦሞ ዞን በግብርና ኢንቨስትመንት በተሰማሩ ባለሃብቶች በ230 ሄክታር መሬት ላይ በሙከራ ደረጃ የለሙ የሩዝ ዝርያዎች ውጤታማ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
በዘርፉ የተሰማሩ የግል ባለሀብቶች የሩዝ ዝርያዎችን በስፋት ቢያለሙ በውጪ ምንዛሬ ከውጭ የሚገባውን የሩዝ ምርት በአገር ውስጥ ምርት መተካት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
በደቡብ ኦሞ ዞን በናይ ጸማይ ወረዳ በግብርና ልማት ላይ የተሰማሩት አቶ ወርቁ ሮሮ፣ ከጂንካ ግብርና ምርምር ማዕከል ባገኙት የዘርና የክህሎት ድጋፍ በሙከራ ደረጃ በ3 ሄክታር መሬት ላይ ሩዝ ማልማታቸውን ጠቁመዋል።
በዚህም 130 ኩንታል የሩዝ ምርት ማግኘታቸውን ጠቅሰው የሩዝ ምርት አዋጭና ጊዜና ጉልበት ቆጣቢ መሆኑን ጠቅሰው በ10 ሄክታር ላይ ለዘር ብዜት የሚሆን ሩዝ እያመረቱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም የጀመሩትን የሩዝ ልማት ስራ የማስፋፋት ዕቅድ እንዳላቸውም አመልክተዋል።