በዲጂታል መታወቂያ ላይ ያለውን የማንነት መረጃ መጠበቅ የሚያስችል የዲጂታል ሰርተፍኬት አገልግሎት ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
በዲጂታል መታወቂያ ላይ ያለውን የማንነት መረጃ መጠበቅ የሚያስችል የዲጂታል ሰርተፍኬት አገልግሎት ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 30/2018(ኢዜአ)፦የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በዲጂታል መታወቂያ ላይ ያለውን የማንነት መረጃ መጠበቅ የሚያስችል የዲጂታል ሰርተፍኬት አገልግሎትን በይፋ አስጀምሯል።
አገልግሎቱ በይፋዊ ቁልፍ መሰረተ ልማት ውስጥ የፋይዳ ደህንነት ማስጠበቂያ ቁልፎች የሚፈጠሩበትና የሚንቀሳቀሱበትን አሰራር ያካተተ ነው ተብሏል።
እነዚህ ቁልፎች በዲጂታል መታወቂያ ላይ ያለውን የማንነት መረጃ ለመጠበቅ ጥቅም ላይ የሚውል የመተማመኛ ዲጂታል ፊርማ ለማዘጋጀት የሚውሉ መሆኑም ተገልጿል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ፤ ከዚህ ቀደም ለኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት የዲጂታል ሰርተፊኬት አገልግሎት መጀመሩን ገልጸው፤ ዛሬ በይፋ የተጀመረው የፋይዳ መታወቂያ ሰርተፊኬት አገልግሎት ቀጣይ ስራ ነው ብለዋል።
የሰርተፊኬት አገልግሎቱ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ በከፍተኛ የደህንነት ደረጃዎች ባላቸው ቴክኖሎጂዎች የተጠበቀ እንዲሆን ያግዛል ነው ያሉት።
የማንነት ስርቆትን ለመከላከል፣ማጭበርበር እና የማንነት መረጃን አላግባብ መጠቀምን ለመከላከል የሚያስችል መሆኑንም አመልክተዋል።
ደህንነቱ የተጠበቀ ዲጂታል መታወቂያ ጤና፣ ትምህርት፣ ባንክን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶች በተሻለ መልኩ ለማግኘት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው መሆኑም ነው የተገለጹት።
የፋይዳን ደህንነት ማረጋገጥ ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ የተሳለጠ አገልግሎት እንዲኖር ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና አስተባባሪ ዮዳሄ አርአያሥላሴ በበኩላቸው፤ 29 ሚሊዮን ዜጎች የፋይዳ መታወቂያ መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
መታወቂያ ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ ደህንነቱን ማስጠበቅ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህ አኳያ የሰርተፊኬት አገልግሎቱ መጀመር ትልቅ እርምጃ ነው ብለዋል።
የሰርተፊኬት አገልግሎቱ የፋይዳ ዲጂታል ሰነዶች ተዓማኒነትን የሚጨምር መሆኑንም ጠቁመዋል።