የመደመር መንግስት ከዲጂታል ተደራሽነት ወደ ጋራ ብልፅግና የተጀመረውን ጉዞ ለማሳካት በትጋት ይሰራል- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግስት ከዲጂታል ተደራሽነት ወደ ጋራ ብልፅግና የተጀመረውን ጉዞ ለማሳካት በትጋት ይሰራል- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 30/2018 (ኢዜአ)፦ የመደመር መንግስት ከዲጂታል ተደራሽነት ወደ ጋራ ብልፅግና የተጀመረውን ጉዞ ለማሳካት፣ በመፍጠር፣ በመፍጠን እና በእመርታ መርሕ በትጋት እንደሚሰራ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ዲጂታል ኢኮኖሚን መገንባት ምርጫ ሳይሆን ብልጫ ነው! በሚል ርዕስ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ዛሬ ሁለተኛውን የኢትዮጵያ ዲጂታል ክፍያ ጉባኤን በይፋ ማስጀመራቸውን ገልጸዋል።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን በውጤታማነት መተግበሩ፣ ለዜጎች ፈጣን፣ ቀልጣፋ እና ወጪ ቆጣቢ አገልግሎቶችን ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር፣ የዕለት ከዕለት የኑሮ እንቅስቃሴን እያቀለለ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በተጨማሪም የኤሌክትሮኒክና የዲጂታል ግብይት ሥርዓትን ተመራጭ የክፍያ መንገድ እንዲሆን ማስቻሉን አመልክተዋል።
ይሄም የሕዝብን ኑሮና የመንግሥትን አገልግሎት ከምርጫም በላይ ብልጫ ያለው እንዲሆን ያስችላል ነው ያሉት።
ባለፉት አምስት ዓመታት በተዘረጋው የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ውስጥ፣ በየዓመቱ ከ18.5 ትሪሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ዝውውር እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ይሄንን ስኬት በላቀ መልኩ በማስቀጠል ሁሉን አቀፍ ብልፅግናን የማሳካት ግብ የያዘውን የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን በቅርቡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት መጽደቁን አውስተዋል።
ስትራቴጂው ዲጂታል መሠረተ ልማትን የማጠናከር፣ ተደራሽነትን ብቻ ሳይሆን አጠቃቀምን ለማስፋት ክሂሎትን የመገንባት እና ችግር ፈቺ ፈጠራን የማበረታታት ዓላማ ያለው መሆኑን ጠቅሰው ለስኬታማነቱ ሁሉም ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር መንግሥት ከዲጂታል ተደራሽነት ወደ ጋራ ብልፅግና የጀመርነውን ጉዞ ለማሳካት፣ በመፍጠር፣ በመፍጠን እና በእመርታ መርሕ ይተጋል ሲሉም ገልጸዋል።