ኢትዮጵያ የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ጠንካራ ዲጂታል ኢኮኖሚ እየገነባች ነው- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ጠንካራ ዲጂታል ኢኮኖሚ እየገነባች ነው- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 30/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ጠንካራ ዲጂታል ኢኮኖሚ እየገነባች መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ፤ ከ2026 - 2030 የሚተገበረውን ብሔራዊ የዲጂታል ክፍያ ስትራቴጂ ይፋ አድርገዋል።
ሁለተኛው የኢትዮጵያ ዲጂታል ክፍያ ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉባኤው መክፈቻ ባደረጉት ንግግር፤ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን በተሳካ ሁኔታ በመተግበር ዘርፈ ብዙ ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ተጨባጭ የዲጂታል እድገት ማስመዝገቧን ጠቅሰው፤ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነት በሚያስደንቅ ፍጥነት መስፋፋቱን ተናግረዋል።
መንግሥት በወሰዳቸው የሪፎርም እርምጃዎች እና የመሠረተ ልማት ግንባታ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ጠንካራ መሠረት መገንባቱን ጠቅሰዋል።
በአሁኑ ወቅት የዲጂታል ፋይናንስ ምህዳሩ በየዓመቱ ከ18 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ብር በላይ ግብይቶችን እያስተናገደ ነው ብለዋል።
የዘርፉ ለውጥ ፈጣንና አስተማማኝ የቴሌኮምና የኢንተርኔት ተደራሽነትን በማስፋት የኢኮኖሚውን ዲጂታል ጉዞ እያፋጠነ መሆኑን ገልጸዋል።
የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ (ፋይዳ) እና መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ያሉ የዲጂታል የመንግሥት አሠራሮች በመቶዎች የሚቆጠሩ አገልግሎቶችን በአንድ ስፍራ በማሳለጥ እንግልትን እየቀነሱና ግልጽነትን እያሻሻሉ መሆኑን ተናግረዋል።
ብሔራዊ ባንክ አሠራሮችን በማዘመን ለሞባይል ገንዘብ ዝውውር፣ ለክፍያ አገልግሎት ሰጪዎች እና ለፈጠራ ባለሙያዎች ምቹ ምህዳር መፍጠሩን ተናግረዋል።
በኢት-ስዊች የተደገፈው ብሔራዊ የዲጂታል ክፍያ አሠራር ከፍተኛ ገንዘብ በባንኮች መካከል እና በዲጂታል አማራጭ በቀላሉ እንዲንቀሳቀስ አስችሏል ነው ያሉት።
የቴሌብር ፈጣን ተደራሽነትና ለአጠቃቀም ምቹ መሆኑ የዕለት ተዕለት የዜጎችን ኑሮ እያሳለጠ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ኢኒሼቲቭን ጨምሮ ዲጂታል ክህሎትን የማጎልበት ሥራዎች ትኩረት እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።
በዲጂታል ዘርፉ የተመዘገቡ ስኬቶች ኢኮኖሚውን ወደ ፊት የሚያሻግሩ ብሔራዊ መሠረተ ልማቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ነገር ግን ከተደራሽነት ባሻገር ትርጉም ባለው አጠቃቀም ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
የዲጂታል አጠቃቀምን ማሳደግ የአርሶና አርብቶ አደሮችን ህይወት በማሻሻል፣ ሥራቸውን በማቅለል፣ የፋይናንስ አገልግሎትን በቀላሉ እንዲያገኙ በማድረግ የአካታች ኢኮኖሚ ዕድገት ይፋጠናል ብለዋል።
የዲጂታል ጉዟችን ቀጣዩ ምዕራፍ ሊለካ የሚገባው የህዝባችንን ህይወት በማሻሻል ረገድ ነው ሲሉም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ከዚህ አኳያ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ መሠረተ ልማትን እንድናጠናክር፣ አጠቃቀምን ማስፋት፣ ክህሎቶችን መገንባት እና ችግሮችን የሚፈታ ፈጠራን የማበረታታት ዓላማ ያነገበ መሆኑን ገልጸዋል።
ዘመኑን የዋጀው ይህ ስትራቴጂ፣ በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ አስተዳደራዊ እና ማህበራዊ ዘርፎች ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ዋነኛ አንቀሳቃሽ ኃይል የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የዲጂታል ግብይት ማህበረሰቡን የሳይበር ደህንነትን በማረጋገጥ ግልጽነት፣ ተጠያቂነት እና ኃላፊነት በተሞላበት አሠራር ህዝቡን ማገልገል እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።
ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በጋራ ዓላማ በማሳተፍ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚሆን ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የዲጂታል መፃኢ ዕድሏን የሚወስን ጠንካራ መሠረት አስቀድማ ገንብታለች ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በቀጣይ ከዲጂታል ተደራሽነት ወደ ተፅዕኖ እና ወደ ጋራ ብልጽግና የሚደረገውን ሽግግር ማፋጠን እንደሚገባ ጠቁመዋል።