ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓም ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓም ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 30፣ 2018(ኢዜአ)፦የዘንድሮው ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓም እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ2018 ዓ.ም ለሚያከናውነው 7ኛው አገራዊ ምርጫ የቅድመ-ምርጫ ተግባራትን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሀን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሀይሉ ቦርዱ እስካሁን በሰራቸው የቅድመ-ምርጫ ሥራዎች እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ገለጻ አድርገዋል።
በዚህም ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች ሲሰሩ ቆይቷል ብለዋል።
ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችን የማደራጀት እንዲሁም የምርጫ ጣቢያዎች ምቹ መሆን የማረጋገጥ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ፕሮግራማቸውን ለህዝቡ የሚያስተዋውቁበት ስልጠና መሰጠቱን ጠቁመዋል።
የእጩዎች ምዝገባ ቦርዱ ባለማው ሶፍትዌር አማካኝነት እንደሚካሄድ ገልጸዋል።
ለዚህም ፓርቲዎች ወይም በግል የሚወዳደሩ ራሳቸውን የመመዝገብ ስራ እንደሚሰሩ ገልጸው፤ ለዚህም ቦርዱ ስልጠና መስጠቱን አመልክተዋል።
እንዲሁም መራጮችም በቦርዱ በለማው ሶፍትዌር እና ከዚህ ቀደም ባለው አሰራር በማኑዋል ምዝገባ እንደሚያካሂዱ ተናግረዋል።
መራጮች ለምዝገባ የሚያቀርቡት መረጃም እንደቀድሞው የሚቀጥል መሆኑን አስታውቀዋል።
የታዛቢ ፈቃድ ለጠየቁም ቦርዱ ባለማው ሶፍትዌር አማካኝነት ፈቃድ ለመስጠት በመጨረሻ ሂደት ላይ እንደሚገኙ ተናግረው፤ ግንቦት 24 ቀን 2018 የድምጽ መስጫ ቀን መሆኑን ጠቁመዋል።
አስቻይ ሁኔታዎችን በተመለከተ ቀጣይነት ያላቸው ውይይቶች ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚደረጉ ተናግረዋል።