ቀጥታ፡

የሊጉ መሪ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከቦሌ ክፍለ ከተማ ጋር ይጫወታል 

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 30/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የ11ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ ይጠናቀቃል። 

ከቀኑ 7 ሰዓት ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከቦሌ ክፍለ ከተማ በአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። 

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሊጉ ያደረጋቸውን 10 ጨዋታዎች አሸንፏል። 28 ግቦችን በጨዋታዎቹ ላይ ሲያስቆጥር አምስት ግቦችን ተቆጥሮበታል። ቡድኑ በ30 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው።

ተጋጣሚው ቦሌ ክፍለ ከተማ በሊጉ ባካሄዳቸው 10 ጨዋታዎች በአራቱ ሲያሸንፍ  ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ አራት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይቷል። 11 ግቦችን ሲያስቆጥር 10 ጎሎችን አስተናግዷል።

ቦሌ ክፍለ ከተማ በ16 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል። 

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ካሸነፈ የሊጉን መሪነት ያጠናክራል። ቦሌ ክፍለ ከተማ ካሸነፈ ተከታታይ ድሉን ያስመዘግባል። 

በሌላኛው መርሃ ግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከድሬዳዋ ከተማ በአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ስታዲየም ይጫወታሉ።

የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሊጉ ባከናወናቸው ስምንት ጨዋታዎች ሰባት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል። በስምንቱ ጨዋታዎች ላይ 26 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ የተቆጠረበት ጎል አንድ ብቻ ነው።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች እየቀሩት በ22 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል። 

ድሬዳዋ ከተማ በሊጉ ባካሄዳቸው 10 ጨዋታዎች አራቱን ሲያሸንፍ በስድስቱ ሽንፈትን አስተናግዷል። 10 ግቦችን ሲያስቆጥር 15 ጎሎችን አስተናግዷል። 

ቡድኑ በ12 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካሸነፈ የሁለተኝነት ደረጃን ከሃዋሳ ከተማ ይረከባል። 

ተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማ በ10ኛ ሳምንት በቦሌ ክፍለ ከተማ ካጋጠመው ሽንፈት በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም