ብክነትን መቀነስ የኃይል አቅርቦትን ማሳደግ፤ የአፍሪካ የኢነርጂ ውጤታማነት አጀንዳ - ኢዜአ አማርኛ
ብክነትን መቀነስ የኃይል አቅርቦትን ማሳደግ፤ የአፍሪካ የኢነርጂ ውጤታማነት አጀንዳ
አፍሪካ በዓለማችን በታዳሽ ኃይል እምቅ ሀብቶችን የያዘች አህጉር ናት። የዓለም 60 በመቶ የፀሐይ ኃይል ሀብት የሚገኘው በአፍሪካ ነው። አህጉሪቱ ከፀሐይ በየዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ቴራዋት ሰዓት ኢነርጂ የማመንጨት አቅም አላት። ይሁንና በፀሐይ የምታመነጨው ኃይል ድርሻ አነስተኛ መሆነን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (ኢሲኤ) የእ.አ.አ 2023 ጥናት ያመለክታል።
የዓለም ባንክ ተቋም የሆነው ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን በበኩሉ አፍሪካ 25 በመቶ የዓለም የንፋስ ኃይል አቅም ያላት ሲሆን 180 ሺህ ቴራ ዋት ሰዓት ማመንጨት እንደምትችል ይገልጻል። ይሁንና በዓለም ላይ በዘርፉ ያላት ድርሻ ከአንድ በመቶ በታች መሆኑን ያነሳል።
ሃይድሮ ፓወር የአፍሪካ ሌላኛው የኢነርጂ ሀብት ማሳያ ነው። የአህጉሪቷ ወንዞች እና ተፋሰሶች በየዓመቱ 1 ሺህ 500 ቴራ ዋት ሰዓት የማመንጨት አቅም ቢኖራም ጥቅም ላይ የዋለው 10 በመቶውን ብቻ ነው። የናይል ተፋሰስ፣ የኮንጎ ተፋሰስ እና የዛምቤዚ ተፋሰሶችን የያዘችው አፍሪካ ከፍተኛ የሃይድሮ ፓወር አቅሟን መጠቀም አልቻለችም ይላል የዓለም አቀፉ የታዳሽ ኃይል ኢነርጂ ኤጀንሲ ጥናት።
ወደ ምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ ያለው የእንፋሎት ኃይል ሌላኛው ትልቅ እድል ነው። የአፍሪካ የእንፋሎት (ጂኦተርማል) አቅም ከ15 እስከ 20 ጊጋዋት መሆኑን የአፍሪካ ኢነርጂ ምክር ቤት መረጃ ያሳያል።
አፍሪካ ከዓለም የኢነርጂ ምርት ውስጥ ከአራት በመቶ በታች እንዲሁም በታዳሽ ኃይል ደግሞ ከ1 ነጥብ 6 በመቶ ያነሰ ድርሻ እንዳላት መረጃዎች ያመለክታሉ።
የአፍሪካ የኢነርጂ ምህዳር ሁለት ተጻራሪ እውነታዎችን የያዘ ነው። አህጉሪቷ የዓለምን 17 በመቶ ህዝብ ብትይዝም በዓለም የኢነርጂ አጠቃቀም ያላት ድርሻ ከአራት በመቶ በታች ነው። በአሁኑ ሰዓት 600 ሚሊዮን ገደማ የሚሆን የአፍሪካ ህዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደማያገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ። 21 በመቶ አፍሪካውያን ብቻ ንጹህ የማብሰያ ነዳጅ እና ቴክኖሎጂዎችን ያገኛሉ። ባህላዊ የምግብ ማብሰያ አማራጮች ለጤና አሉታዊ ተጽእኖ የሚያሳድሩ ናቸው።
በአፍሪካ ከከተሜነት መስፋፋት እና ከፈጣን የህዝብ እድገት ጋር በተያያዘ የኢነርጂ ፍላጎት በፍጥነት እየጨመረ ይገኛል። እ.አ.አ በ2040 የአፍሪካ ህዝብ 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ህዝብ እንደሚያልፍ ትንበያዎች ያሳያሉ። በተለይም የህዝብ ብዛት መጨመሩ በኢነርጂ አቅርቦት ላይ ጫና ያሳድራል።
ከእ.አ.አ 2014 እስከ 2023 የአፍሪካ የታዳሽ ኢነርጂ በእጥፍ አድጎ ከ32 ነጥብ 5 ጊጋ ዋት ወደ 62 ነጥብ 1 ጊጋ ዋት ማደጉ መልካም የሚባል እምርታ መሆኑን የዓለም አቀፉ የታዳሽ ኃይል ኢነርጂ ኤጀንሲ ይገልጻል።
የአፍሪካ ሌላኛው ፈተና የምትጠቀመውን ኢነርጂ የብክነት ምጣኔ ነው። በበቂ ሁኔታ ባልተደራጀው የኢነርጂ ስርዓት ምክንያት አፍሪካ በየዓመቱ በቢሊዮን ዶላሮች የሚገመት ገንዘብ ታጣለች።
እንደ ዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ መረጃ ከሆነ አፍሪካ የኢነርጂ አጠቃቀሟን የምታሻሽል ከሆነ 30 በመቶ የኢነርጂ ወጪዋን መቀነስ ትችላለች። ይህም የአፍሪካ መንግስታት ለማህበራዊ ልማት የሚያወጡትን በጀት እንደሚያሳድግ እና አዲስ የኃይል ማመንጫዎችን ሳትገነባ የካርቦን ልቀትን መቀነስ የምትችልበትን እድል ይፈጥርላታል።
ኢትዮጵያ ከወራጅ ወንዞች በአመት 124 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ያላት ሲሆን ከ36 እስከ 40 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የከርሰ ምድር የውሃ ሃብት እንዳላት የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።
ከገፀ ምድር የውሃ ሃብቷ 83 በመቶ የሚገኘው ከተከዜ፣ ባሮ፣ አባይና ጊቤ ኦሞ ወንዞች ነው። አንዱ የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚመነጨው ካላት የውሃ ሀብት ነው።
ኢትዮጵያ በውሃ፣ በፀሐይ፣ በነፋስ እና በጂኦ-ተርማል የኃይል አማራጮች በአጠቃላይ ከ300 እስከ 400 ጊጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳላት መረጃዎች ያሳያሉ።
በ10 ዓመት መሪ ልማት እቅዱ ኢትዮጵያ አሁን እያመነጨች ያለውን 4 ሺህ 818 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ 17 ሺህ ሜጋ ዋት ለማሳደግ አቅዳለች።
ከለውጡ በኋላ በኢነርጂው ዘርፍ ያለውን አቅም ለመጠቀም የተለያዩ የማሻሻያ ስራዎች ተከናውነዋል።
ከስራዎቹ መካከል ለሶስት አስርት ዓመታት ስራ ላይ የነበረውን የኢነርጂ ፖሊሲ ማሻሻል ይገኝበታል።
ፖሊሲው ከ2013 ዓ.ም አንስቶ የማሻሻያ ዝግጅት ሲደረግበት ቆይቷል። የፖሊሲ ማሻሻያው የተዘጋጀው አሁን ያለውን ሀገራዊ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ ነባራዊ እውነታ መሰረት ባደረገ መልኩ ነው።
ለኢነርጂ ፖሊሲው ማሻሻል ምክንያቶች ከሆኑት መካከልም ከሀገር በቀል ኢኮኖሚ፣ ከአረንጓዴ ልማት፣ ከ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድና ከዘላቂ የልማት ግቦች ጋር ማጣጣም በማስፈለጉ እንደሆነም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመረቀው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብም በአፍሪካ ግዙፉ የኢነርጂ ፕሮጀክት ሲሆን ለቀጣናው እና ለአፍሪካ ሀገራት ትልቅ አቅምን ይዞ መጥቷል።
ከፖሊሲው ትኩረት አንዱ ከአገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት ለጎረቤት አገራት ኃይል በማቅረብ ቀጣናዊ ትስስርን ማጠናከር እንደሆነም በሰነዱ ላይ ሰፍሯል።
በ10 ዓመቱ የመሪ ልማት እቅዱም ዜጎችን በስፋት የአሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ የማድረግ ግብ ተይዟል። ከዚህ ባሻገር በእቅዱ ኢትዮጵያ የቀጣናው ሀገራትን በኃይል የማስተሳሰር ዕቅድ ሰንቃ እየሰራች ትገኛለች።
በእቅዱ ለጎረቤት አገራት እየቀረበ ያለውን 2 ሺህ 803 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ወደ 7 ሺህ 184 ጊጋ ዋት ሰዓት የማሳደግ ውጥን ተይዟል።
የአፍሪካ የኢነርጂ አጠቃቀምን ለማሻሻል እና ብክነትን ለመቀነስ የተቀናጀ ምላሽ የመስጠት ጉዳይ ጊዜ የማይሰጠው ነው።
የአፍሪካ ህብረት ያዘጋጀው የመጀመሪያው አህጉራዊ የኢነርጂ ውጤታማነት ኮንፍረንስ (Energy Efficiency Conference) ታህሳስ 2 እና 3 ቀን 2018 ዓ.ም በህብረቱ ዋና መቀመጫ በአዲስ አበባ ይደረጋል።
ኮንፍረንሱ እ.አ.አ በ2024 በአዘርባጃን ባኩ በተካሄደው 29ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ-29) ይፋ የተደረገው የአፍሪካ ኢነርጂ ውጤታማነት ጥምረት ማዕቀፍ ስር የሚካሄድ ነው።
የጥምረቱ ማዕቀፍ በአፍሪካ ህብረት ስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መጽደቁ ይታወቃል።
“የአፍሪካ የኢነርጂ ውጤታማነት አጀንዳን በስትራቴጂካዊ አጋርነት ውጤታማ ማድረግ” የኮንፍረንሱ መሪ ሀሳብ ነው።
አህጉራዊው ሁነት የተዘጋጀው የአፍሪካ ህብረት ልዩ ተቋም በሆነው የአፍሪካ ኢነርጂ ኮሚሽን እና በኢትዮጵያ መንግስት ትብብር ነው።
ኮንፍረንሱ የኢነርጂ ውጤማነትን በማረጋገጥ የአፍሪካ ኢኮኖሚ እድገት፣ ዘላቂ ልማት እና ለአየር ንብረት ለውጥ የተግባር ምላሽ አቀጣጣይ ሞተር የማድረግ አላማ ያለው መሆኑ ተገልጿል።
የአፍሪካ ኢነርጂ ኮሚሽን ዋና ዳይሬክተር ራሺድ አሊ አብደላ ኮንፍረንሱን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት የኢነርጂ ውጤማነት የአፍሪካ ዘላቂ ልማት ዋንኛ ሀብት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የኢነርጂ ውጤማነት የኃይል ብክነት፣ የካርቦን ልህቀት እና ወጪ ለመቀነስ እንዲሁም ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ እድገት ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ኮንፍረንሱ የአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ አመራሮች፣ ሚኒስትሮች፣ የኢንዱስትሪ መሪዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ የግሉ ዘርፍ፣ የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት ፣ ተመራማሪዎች እና ባለሙያዎችን በአንድ መድረክ የሚያገናኝ ነው።
ባለድርሻ አካላቱ በአፍሪካ ዘላቂ የኢነርጂ ትራንስፎርሜሽንን ለማፋጠን የሚያስችሉ ውጤታማ የኢንቨስትመንት አማራጮችና ፖሊሲዎች ላይ በመምከር ቀጣይ ስራዎች ላይ የጋራ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጡ ኢዜአ ከአፍሪካ ህብረት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
የአፍሪካ ከፍተኛ እና በሰፊው ጥቅም ላይ ያልዋለ የታዳሽ ኢነርጂ አቅም በቀጣይ የዓለም የኢነርጂ ሽግግር እና አቅርቦት ውስጥ ትልቅ ሚና የሚጫወት ነው። የኢነርጂ አቅሙን ትሩፋቶች የመጠቀም ጉዳይ አነስተኛ ነው ማለት ይቻላል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ያላቸውን የታዳሽ ኃይል ምንጭን ለመጠቀም እየወሰዷቸው የሚገኟቸው እርምጃዎች ተስፋ ሰጪ ናቸው።
የኢነርጂ ውጤታማነትን ማሳደግ፣ የተቀናጁ ፖሊሲዎች፣ የተቀናጀ ቀጣናዊ የኃይል ቋቶችን መፍጠር፣ የኢነርጂ ፋይናንስን ማሳደግ እና የመንግስታት የፖለቲካ ቁርጠኝነት የአፍሪካ ኢነርጂ አቅሞች ወደ ዘላቂ ልማት፣ የኢነርጂ ደህንነት የማረጋገጥ፣ የአየር ንብረትን የሚቋቋም ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባትን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ትሩፋቶች ይዞ ይመጣል።