አዲሃን ለሀገር ብሄራዊ ጥቅምና ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የድርሻውን እንደሚወጣ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
አዲሃን ለሀገር ብሄራዊ ጥቅምና ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የድርሻውን እንደሚወጣ ገለጸ
ባሕር ዳር፤ ሕዳር 29/2018(ኢዜአ)፦ የአማራ ዲሞክራሲያዊ ሃይሎች ንቅናቄ (አዲሃን) ለሀገር ብሄራዊ ጥቅምና ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የድርሻውን የሚወጣ መሆኑን ገለጸ።
የአማራ ዲሞክራሲያዊ ሃይሎች ንቅናቄ (አዲሃን) ለሁለት ቀናት ያካሄደውን 3ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ማጠናቀቁን ተከትሎ የንቅናቄው የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ ራስወርቅ መላኩ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ፓርቲው በሰላማዊ ትግል ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መጎልበት የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ፓርቲው ለሀገር ብሄራዊ ጥቅምና ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የድርሻውን የሚወጣ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
የፓርቲው የጥናትና ምርምር ሃላፊ አዲሱ ጉልላት (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ለዴሞክራሲ ስርዓት መጠናከር እንዲሁም ለሰላምና የልማት ስራዎች የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል።
በጉባኤው የአመራሮችን ምርጫ በማካሄድ ፓርቲውን አቶ ተስፋሁን አለምነህ በሊቀመንበርነት እንዲሁም አዳነ ወዳጀነህ (ዶ/ር) በምክትል ሊቀመንበርነት እንዲመሩ መርጧል።
በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና በአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት (አፋህድ) መካከል ዘላቂ የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ የኃይል አማራጭ ተቀባይነት እንደሌለው ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ተስፋሁን አለምነህ መግለፃቸው ይታወሳል።