የመንግስት የልማት ኢኒሼቲቮችን በውጤታማነት በመምራትና በመተግበር ለለውጥና እድገት እንተጋለን--ሰልጣኝ አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
የመንግስት የልማት ኢኒሼቲቮችን በውጤታማነት በመምራትና በመተግበር ለለውጥና እድገት እንተጋለን--ሰልጣኝ አመራሮች
ሚዛን አማን/ቦንጋ፤ ኅዳር 29/2018 (ኢዜአ)፡-የመንግስት የልማት ኢኒሼቲቮችን በውጤታማነት በመምራትና በመተግበር ለአካባቢው ለውጥና ዕድገት በትጋት እንደሚሠሩ የቤንች ሸኮ ዞን አመራሮች ገለጹ።
በካፋ ዞን በመደመር እሳቤ እየተከናወኑ የሚገኙ የተለያዩ የልማት ሥራዎች ህብረተሰቡን በተጨባጭ ተጠቃሚ ያደረጉ መሆኑም ተመላክቷል።
"በመደመር መንግሥት እይታ የዘርፎች እምርታ" በሚል መሪ ሀሳብ በቤንች ሸኮ እና ካፋ ዞኖች በተሰጠ ስልጠና የተሳተፉ አመራሮች የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
በዚህም አመራሮቹ የገጠርና ከተማ ኮሪደር ልማት ሥራ፣ የሌማት ትሩፋት እንቅስቃሴ፣ የማኑፋክቸሪንግ ሥራዎችና ሌሎች የልማት ሥራዎችን ተመልክተዋል።
በቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ እና ሚዛን አማን ከተማ በተካሄደ ጉብኝት የተገኙ አመራሮች የመንግስት የልማት ኢንሼቲቮችን በውጤታማነት በመምራትና በመተግበር ለአካባቢው ለውጥና እድገት ጠንክረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
ከሰልጣኝ አመራሮች መካከል ከደቡብ ቤንች ወረዳ የመጡት አቶ ዳንኤል ማርቆስ እንዳሉት አካባቢው ለኢኮኖሚ ምንጭ የሆኑ የተለያዩ ሀብቶች ቢኖሩትም ለይቶ ማልማት ባለመቻሉ ተገቢውን ጥቅም ማግኘት አልተቻለም።
በመንግስት የልማት አቅጣጫዎችና ባገኙት ስልጠና ሀብቶችን ለይቶ ማልማት የሚቻልበት አቅም እያገኘን በመሆኑ በቁርጠኝነት ወደ ተግባር እንገባለን ብለዋል።
በተለይ የከተማና የገጠር ኮሪደር፣ የሌማት ትሩፋት ሥራና ሌሎች ሀገራዊ ኢኒሺየቲቮች የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በመሆናቸው እነዚህን አጠናክሮ በማስቀጠል እድገትን ለማፋጠን እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
እንደ አመራር ሠርቶ የማሰራት ልምድን በማዳበር ለሕዝቡ አርዓያ መሆን አለብን ያሉት ደግሞ ከጉራ ፈርዳ ወረዳ የመጡት ወይዘሮ ባኒ ሀየች ናቸው።
በምልከታ ወቅት ያየናቸው የግብርና ልማት ሥራዎች በምግብ ራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት ትልቅ ትርጉም ያላቸው በመሆኑ በቀጣይ ሳይለማ የሚቀር መሬት እንዳይኖር እንተጋለን ብለዋል።
ከሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር የመጡት አቶ ንጉሤ ሳፕምቴት የተባሉ አመራር በበኩላቸው በተግባር የተደገፈው ሥልጠና በተከናወኑ የልማት ሥራዎች የተገኙ ውጤቶችን ለማስቀጠል ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ አመራር የሀሳብና የተግባር አንድነት በመያዝ ለአካባቢው የብልጽግና ጉዞ መፋጠን ምቹ ሁኔታ እንፈጥራለን ሲሉ አክለዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የቤንች ሸኮ ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደግፌ ኩድን በበኩላቸው አመራሩ በንድፈሀሳብ ያገኘውን ስልጠና በተግባር እንዲያረጋግጥ ታስቦ የመስክ ምልከታ መደረጉን ተናግረዋል።
የተጀመሩ የልማት ኢኒሼቲቮች ውጤት እየተመዘገበባቸው በመሆኑ በቀጣይ አጠናክሮ ለማስቀጠል ይሰራል ብለዋል።
በተመሳሳይ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል እየተሰጠ ባለው ሦስተኛ ዙር ስልጠና እየተሳተፉ ያሉ የካፋ ዞን መካከለኛ አመራሮች በዞኑ ሺሾእንዴ ወረዳና ሺሽንዳ ከተማ ዛሬ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው አመራሮችም በመደመር እሳቤ በዞኑ እየተከናወኑ ያሉ የተለያዩ የልማት ሥራዎች ህብረተሰቡን በተጨባጭ ተጠቃሚ ያደረጉ ስለመሆኑ መመልክታቸውን ተናግረዋል።
ከካፋ ዞን ቢጣ ወረዳ የመጣቱ አቶ ገላዬ ወዳጆ በስልጠና ቆይታቸው በንድፈ ሀሳብ ያገኙትን እውቀት በተግባር መሬት ላይ መመልከታቸው ለቀጣይ ስራ ተጨማሪ አቅም እንደሆናቸው ገልፀዋል።
በጉብኝቱ በሌማት ትሩፋት በማር፣ በዓሣና ሌሎች የልማት ዘርፎች የተመለከቷቸው ውጤታማ ተግባራት የህብረተሰቡን ሕይወት ያሻሻሉና የስራ ባህልንም የቀየሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ከጨና ወረዳ የመጡት አቶ ቻለው ሀይሌ በበኩላቸው በኢንዱስትሪ፣ በከተማ ልማት፣ በቱሪዝምና በማዕድን ዘርፍ የተሰጠው ስልጠና እይታቸውን የቀየረና ለተሻለ ሥራ ያነሳሳቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በመስክ የተመለከቷቸው ውጤታማ የልማት ሥራዎች የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት እያረጋገጡ በመሆኑ እንደ አመራር አጠናክሮ ለማስቀጠል ጠንክረው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
አመራሮቹ ከስልጠናው ያገኙትን እውቀት ተጠቅመው በቀጣይ በቁጭት መንፈስ በመስራት በየዘርፉ እምርታን ለማምጣትና የህዝብን ተጠቃሚ ለማሳደግ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።