በዓሉ የኢትዮጵያን መልክ ያየንበትና የደመቀ ነው -የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ተሳታፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
በዓሉ የኢትዮጵያን መልክ ያየንበትና የደመቀ ነው -የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ተሳታፊዎች
ሆሳዕና ፤ ሕዳር 29/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል የኢትዮጵያን ትክክለኛ መልክ ያየንበትና የደመቀ ነው ሲሉ የበዓሉ ተሳታፊዎች ተናገሩ።
20ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በደመቀ ሁኔታ ዛሬ በሆሳዕና ከተማ ተከብሯል።
ከተለያዩ አካባቢዎች በመምጣት በበዓሉ የታደሙ ተሳታፊዎች እንዳሉት፤ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል የኢትዮጵያን ትክክለኛ መልክ ያዩበትና በደመቀ ሁኔታ ተከብሯል።
ከትግራይ ክልል የመጣችው ወጣት ራሄል ገብረሚካኤል በሰጠችው አስተያየት እኛ ኢትዮጵያውያን በአብሮነትና በትብብር ስንጓዝ የተለየ ውበት እንዳለን በበዓሉ አከባበር ላይ ተመልክቻለሁ ብላለች።
በዓሉን ኢትዮጵያን በሚገልጹ የተለያዩ ማንነቶች በደመቀና ባማረ መልኩ ማክበራቸውን የተናገሩት ደግሞ ከሲዳማ ክልል የተሳተፉት አቶ አስናቀ አየለ ናቸው፡፡
በዓሉ ባህልና ትውፊቶችን ለመለዋወጥ ዕድል ከመፍጠሩ ባሻገር የአብሮነት እሴቶች እንዲጠናከሩ ሚናው የማይተካ ነው ብለዋል።
ከአፋር ክልል በቀኑ አከባበር ላይ የተሳተፈው ወጣት አሊሚራሀ አህመድ በበኩሉ በሆሳዕና ከተማ የበዓሉ አከባበር የተለየ መሆኑን አንስቶ፤ ከእንግዳ አቀባበል ጀምሮ የአብሮነትና ኢትዮጵያዊነት እሴት የተንፀባረቀበት በመሆኑ መደሰቱን ገልጿል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የተጀመረውን ሁለንተናዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ለማጠናከር እንዲህ ያሉ ህብረ-ብሔራዊ በዓላት አበርክቷቸው የጎላ መሆኑንም ነው የተናገረው፡፡
"የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ከውበትነት ባለፈ አብሮነትን በማጠናከር ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በማጠናቀቅ ሀገር ለመለወጥ አቅም እየሆነ መጥቷል" ሲሉ የተናገሩት ደግሞ ከስልጤ ዞን የታደሙት ይርዳው ናስር (ዶ/ር)ናቸው፡፡
በዓሉ አብሮነትን ከማጠናከር በተጨማሪ ለሀገረ መንግሥት ግንባታው መጠናከር ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልፀዋል፡፡