የኢትዮጵያን ምርቶች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የሚያሳድጉ የጥራት ፍተሻ ላቦራቶሪዎች በክልሎች ይተከላሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ምርቶች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የሚያሳድጉ የጥራት ፍተሻ ላቦራቶሪዎች በክልሎች ይተከላሉ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 29/2018(ኢዜአ)፦ በሁለተኛው ምዕራፍ የብሔራዊ ጥራት መሠረተ ልማት ፕሮጀክት የኢትዮጵያን ምርቶች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የሚያሳድጉ ላቦራቶሪዎች ተከላ በክልሎች እንደሚከናወን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።
ባለፉት ስምንት ዓመታት ሲተገበር የነበረው የመጀመሪያው ምዕራፍ ብሔራዊ የጥራት መሰረተ-ልማት ፕሮጀክት መጠናቀቁ ዛሬ በአዲስ አበባ በተካሄደ መርኃ ግብር ይፋ ተደርጓል።
የንግድና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፥ የብሔራዊ የጥራት መሠረተ-ልማት ፕሮጀክት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት ከስምንት ዓመታት በፊት መጀመሩን አስታውሰዋል።
በመንግስትና በዓለም ባንክ የ50 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ በተመረጡ ሦስት ዘርፎች ላይ ሲተገበር የቆየው ብሔራዊ የጥራት መሠረተ ልማት ፕሮጀክት ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል።
የጥራት መሠረተ ልማት በኢትዮጵያ እያደገ ለመጣው የንግድና የኢንቨስትመንት ዘርፍ ጉልህ ሚና መጫወቱንም አንስተዋል።
የብሔራዊ የጥራት መሠረተ ልማት ፕሮጀክት ኢትዮጵያን የሚመጥን ተቋም በመገንባት የወጪና ገቢ ምርቶች ተወዳዳሪነትና ተፈላጊነት እንዲጨምር ማድረጉንም ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቱ ከሀገራዊ የኢንዱስትሪዎች ዕድገት እቅድ ጋር ተጣጥሞ የተተገበረ በመሆኑ ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የተጀመረውን ጥረት በመደገፍ ረገድ ገንቢ ሚና መጫወቱን አመልክተዋል።
በመጀመሪያው ምዕራፍ የፕሮጀክት ትግበራ የተገኙ ውጤቶችን በዘላቂነት ለማስቀጠልና አዳዲስ ዘርፎችን ለመጨመር የፕሮጀክቱ ሁለተኛው ምዕራፍ በቅርቡ ይጀመራል ብለዋል።
ሁለተኛው ምዕራፍ የብሔራዊ ጥራት መሠረተ ልማት ፕሮጀክት ኢትዮጵያን በዓለም ተወዳዳሪ የሚያደርጉ ላቦራቶሪዎች ተከላን ጨምሮ የሰው ኃይል አቅም ግንባታ ላይ ትኩረት እንደሚደረግም ነው ሚኒስትሩ ያመለከቱት።
ለዚህም የጥራት ጉዳዮችን በስርዓተ ትምህርት አካትቶ ከመተግበር በተጓዳኝ የላቦራቶሪ ተከላ ሥራዎች ከፌዴራል ባለፈ በቅርንጫፎችና በክልሎች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መሠረት በቀለ(ዶ/ር) ፕሮጀክቱ የባለሙያዎችን አቅም ለመገንባት የጎላ አስተዋጽኦ እንዳበረከተላቸው አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሙሉጌታ ደርበው (ዶ/ር) የጥራት ቁጥጥር ላቦራቶሪዎች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲከናወኑ ፕሮጀክቱ ጉልህ ሚና ተጫውቷል ነው ያሉት።