በባሌ ዞን በግብርናው ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶች የብልጽግና ጉዞ ስኬት ማሳያዎች ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በባሌ ዞን በግብርናው ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶች የብልጽግና ጉዞ ስኬት ማሳያዎች ናቸው
ሮቤ፤ ህዳር 29/2018(ኢዜአ)፡-በባሌ ዞን ግብርናው ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶች የብልጽግና ጉዞ ስኬት ማሳያዎች መሆናቸውን በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር መንግስቱ በቀለ ገለጹ።
ዶክተር መንግሥቱና ሌሎች ከፍተኛ የክልሉና የዞኑ የሥራ ኃላፊዎች በባሌ ዞን ሲናና ወረዳ በኩታ ገጠም እየለማ የሚገኘውን የነጭ ሽንኩርትና ሌሎች ገበያ ተኮር ምርቶችን ጎብኝቷል።
ኃላፊው ዶክተር መንግሥቱ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ የክልሉ መንግሥት የአርሶ አደሩን ህይወት ለመለወጥ የተለያዩ ኢኒሼቲቮችን ተግባራዊ እያደረገ ነው።
በዚህም በባሌ ዞን ከ80 በመቶ አርሶ አደሮች የኩታገጠም አሰራርን ተግባራዊ በማድረግ ስንዴና ሌሎች ሰብሎችን እያለሙ መሆናቸውን አመልክተዋል።
በዞኑ የሲናና ወረዳ አርሶ አደሮች ከመደበኛው የሰብል ልማት በተጓዳኝ እያከናወኑ የሚገኙት ገበያ ተኮር ነጭ ሽንኩርትና ሌሎች ኢኒሼቲቮች የጥረቱ ማሳያዎች ናቸው ብለዋል።
አርሶ አደሮች የውኃ አማራጮችን በመጠቀም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ገበያን ለማረጋጋት የሚያግዙ አትክልቶች ማልማታቸውን አመልክተዋል።
በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አካላት ለአርሶ አደሩ የገበያ ትስስር ለመፍጠር መሰራቱን ተናግረዋል ።
የባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሀኪም አልይ በበኩላቸው፣ በዞኑ በመኸር ወቅት 528 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ የሰብል አይነቶች ለምቷል ብለዋል።
የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን በመጠቀም ከለማው መሬት መካከል 400 ሺህ ሄክታሩ በኩታ ገጠም አሰራር የለማ መሆኑን ተናግረዋል።
በዞኑ በመኽሩ ወቅት አርሶ አደሩ ከመደበኛው የሰብል ልማት በተጓዳኝ ነጭ ሽንኩርትን ጨምሮ ሌሎች ገበያ ተኮር አትክልቶችን ከ22 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ እያለማ መሆኑን ገልጸዋል።
በወረዳው በመኽሩ ሰብል ከለማው 70 ሺህ ሄክታር መካከል 2 ሺህ የሚሆነው በነጭ ሽንኩርት ብቻ የለማ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሲናና ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሁሴን ሂኮ ናቸው።
ከሲናና ወረዳ አርሶ አደሮች መካከል ሐጅ ሳፊ በከር እንደተናገሩት ባለፉት ዓመታት ከምርምር ማዕከላት የሚለቀቁ የተሻሻሉ የስንዴ ምርጥ ዘር ሙሉ የግብርና ፓኬጅን በመተግበር ከአንድ ሄክታር እስከ 70 ኩንታል ማምረታቸውን ተናግረዋል ።
እንዲሁም ከመደበኛው የሰብል ልማት በተጓዳኝ ከአካባቢያቸው አርሶ አደሮች ጋር በመቀናጀት በ3 ሄክታር ማሳቸው ላይ ከሚያመርቱት ነጭ ሽንኩርት በአንድ የምርት ወቅት ብቻ የተሻለ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት ባገኙት ተጨማሪ ገቢም በባሌ ሮቤና ሌሎች ከተሞች ላይ ደረጃውን የጠበቀ የመኖሪያ ቤት በመገንባት የተሻለ ህይወት እየመሩ መሆናቸውን አስተውሰዋል።
የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ጉብኝት እያመረትን ለሚገኘው ሽንኩርትና ሌሎች ሰብሎች የተሻለ ገበያ እንድናገኝ ትስስር እንዲፈጠርልን ያግዘናል ያሉት ደግሞ ሌላው የወረዳ አርሶ አደር ከበደ ተፈራ ናቸው።
የእርሻ ሥራቸውን በትራክተር በማረስ ምርታማነታቸውን ከማሳደግ አልፈው ለሌሎችም አርሶ አደሮች ጭምር መትረፋቸውን አመልክተዋል።