ቀጥታ፡

የስንዴ ልማቱ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለተያዘው  ትልም መሳካት ትልቅ  ማሳያ ነው - የአመራር አባላት

ወላይታ፤ ሕዳር 29/2018 (ኢዜአ)፦ እየተከናወነ የሚገኘው የስንዴ ልማት የምግብ ዋስትናን በአጠረ ጊዜ ማረጋገጥ እንደሚቻል ትልቅ ማሳያ መሆኑን በወላይታ ዞን ስልጠና ሲከታተሉ የቆዩ መካከለኛና ከፍተኛ አመራር አባላት ተናገሩ።

"በመደመር መንግሥት ዕይታ የዘርፎች እመርታ" በሚል መሪ ሃሳብ በዞኑ ስልጠና ሲከታተሉ የቆዩ መካከለኛና ከፍተኛ አመራር አባላት በቦዲቲ ከተማ እና በዳሞት ጋሌ ወረዳ የስንዴ ልማት፣ የኢንዱስትሪ፣ የኮሪደርና ሌሎች የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።

የአመራር አባላቱ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለፁት፤ እየተከናወኑ የሚገኙ የስንዴ ልማት ስራዎች የምግብ ዋስትናን በአጠረ ጊዜ ማረጋገጥ እንደሚቻል ማሳያ ነው።

አስተያየታቸውን ከሰጡ የአመራር አባላት መካከል ወይዘሮ መሰረት ሆጃሞ ስልጠናው ከመናገር በላይ ሰርተን ለመለወጥ የሚያስችል መስፈንጠሪያ አቅምን አግኝተንበታል ብለዋል።

በሁሉም ዘርፎች እየመጡ ያሉ ውጤቶች የሚያስደስቱ መሆናቸውንና በስንዴ ልማቱ የተመዘገበው ስኬት በምግብ ሰብል ራስን ለመቻልና ከተመጽዋችነት ለመውጣት የተያዘው ውጥን እንደሚሳካ ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በመሆኑም በስልጠናውም ሆነ በጉብኝቱ ያገኙትን አቅም በማቀናጀት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት ለመስራት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ስልጠናው አመራሩ ሀገሩን አውቆ አቅሙን እንዲያወጣ ያግዛል ያሉት ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ አንዱዓለም ጌታሁን በወረዳው ያዩት ልማት ለሀገር ትልቅ ተስፋ ነው  ብለዋል።

በወረዳው አርሶ አደሩ በክላስተር በመደራጀት እያለማ የሚገኘው የስንዴ ልማት ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጥ መሆኑን ተመልክተናል ብለዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የወላይታ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አማረ አቦታ (ዶ/ር) በዞኑ በግብርናው፣ በኢንዱስትሪው፣ በከተማ ልማትና በቱሪዝም እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል። 

ስልጠናውም በአመራሩ ዘንድ ቁጭት በመፍጠር የህዝቡን መሠረታዊ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ ተግቶ እንዲሰራ አቅም የሚፈጥር እንደሆነም ገልፀዋል።

ያሉ ፀጋዎችን አሟጦ በመጠቀም የግብርናን ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ከዚህ ቀደም ምርት የማይሰጡ ማሳዎችን በኖራ በማከም፣ በመስመር በመዝራትና ግብዓት በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን የመጨመር ስራ መሰራቱንም አስረድተዋል።

ሰልጣኝ አመራር አባላቱ ያገኙትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ተግዳሮቶችን ወደ ዕድል በመቀየር በየአካባቢው ያሉ እምቅ ፀጋዎችን በማልማት በሁሉም ዘርፎች እመርታ ለማስመዝገብ መትጋት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም