ቀጥታ፡

የብረታ ብረት ኢንዱስትሪው እያመጣ ያለው ለውጥ የገጠርና የከተማ ትራንስፎርሜሽን ለማረጋገጥ የሚያግዝ ነው

ባሕርዳር፤ ሕዳር 29/2018(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የብረታ ብረት ኢንዱስትሪው  ዘርፍ እያመጣ ያለው ለውጥ  የተጀመረውን የገጠርና የከተማ ትራንስፎርሜሽን ለማረጋገጥ የሚያግዝ መሆኑ ተገለጸ።

በክልሉ  ያሉ የሚዲያና የሕዝብ ግንኙነት አመራሮችና ባለሙያዏች  የመንግስት የልማት ድርጅት  የሆነውን የአማራ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪና ማሽን ቴክኖሎጅ ኢንተርፕራይዝን  ዛሬ ተዘዋውረው ተመልክተዋል። 

ዓላማውም የሚዲያና የሕዝብ ግንኙነት አመራሩና ባለሙያው በዘርፉ የገበያ  ትስስር ለመፍጠር እየተሰራ ያለውን ተግባር  በማገዝ ሚናቸውን እንዲወጡ ለማነሳሳት እንደሆነ ተነግሯል።


 

በዚህ ወቅት የክልሉ  መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ አባይ መንግስቴ  እንዳሉት፤ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን  አቅም  በማሳደግ  እድገቱን ለማፋጠን እየተሰራ ይገኛል።

በተለይም የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት ለማሳደግና ከተሞችን ለማዘመን ቴክኖሎጂ ላይ መስራት መጠየቁን አስረድተዋል።

ይህንን ለማሳካት የብረታ ብረት ኢንዱስትሪው ዘርፍ እየመጣ ያለውን ለውጥ  የገጠርና የከተማ ትራንስፎርሜሽን ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ  ገልጸዋል።

በዚህም የአማራ ብረታ ብረትና ማሽን ቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዝ የኢንዱስትሪ መለዋወጫዎችን፣ አነስተኛ ማሽኖችን፣ ስማርት ፖሎችንና ሌሎች ግብአት እያመረተ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢንተርፕራይዙ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ዘላለም በላይ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ኢንተርፕራይዙ የአምራች ኢንዱስትሪውን ችግር ለማቃለል እየሰራ ይገኛል።

ለአብነትም  የፋብሪካዎችን መለዋዎጫዎች በማምረት የኢንዱስትሪውን  ዘርፉ   እያሳደገ  መሆኑን አንስተዋል።

ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪና ፋብሪካዎች ግብአት አምርቶ በማቅረብ የክልሉን ብሎም የሀገሪቱን   እድገት ለማፋጠን ኢንተርፕራይዙ የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ኢንተርፕራይዙ ከሚያመርታቸው ውስጥ ትራንስፎርመር፣ ማረሻ፣ ተንጠልጣይ ድልድይ እና ስማርት ፖል እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል። 

ቴክኖሎጅን የማላመድ፣ የመፍጠርና የማበዛት ስራ በማከናወን  የውጭ ምንዛሬን ለማዳን  ትኩረት መስጠቱን አመልክተዋል።

በቀጣይ የውሃ ፓንፕ፣ የመኖ ማቀነባበሪያ፣ አነስተኛ ትራክተር፣ የበቆሎ መፈልፈያና ሌሎች ማሽነሪዎችን ለማምረት አቅዶ ወደ ተግባር መግባቱንም ጠቁመዋል። 

ኢንተርፕራይዙ ለ600 ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም