ቀጥታ፡

የልማት ፀጋዎችን ወደ ውጤት በመቀየር የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንሰራለን

ቦንጋ ፤ ሕዳር  29/2018 (ኢዜአ)፡-የልማት ፀጋዎችን ወደ ውጤት በመቀየር የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በቁጭት እንደሚሰሩ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አመራሮች ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በከፍተኛ አመራሮች ስልጠና ማጠቃለያ ላይ አመራሩ ብልጽግናን ለማረጋገጥ  በሚደረገው ጥረት በመፍጠን፣ በመፍጠር፣ በማባዛትና በማጥራት መስራት እንዳለበት መመሪያ መስጠታቸው ይታወሳል። 

በስልጠናው ኢዜአ ያነጋገራቸው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አመራሮችም ስልጠናው በየአካባቢው ያሉ የልማት ፀጋዎችን ወደ ውጤት በመቀየር የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ አቅም እንደሆናቸው ገልጸዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የካፋ ዞን ንግድና ኢንቨስትመንት መምሪያ ምክትል ሀላፊ አቶ ሀብታሙ ገብረስላሴ እንደገለጹት በክልሉ ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶችን አልምቶ ለኢንቨስትመንት ለማዋል ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በቀጣይ በሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ላይ ፈጠራና ፍጥነት በማከል የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በስልጠናው ያገኙትን አቅም ወደተግባር እንደሚቀይሩ አረጋግጠዋል።

በዞኑ ኢንቨስትመንትን በመሳብ የግል ባለሀብቱን ተሳትፎ ለማሳደግና የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቁጭት ይሰራል ሲሉም ገልጸዋል።

ሌላው አስተያየት ሰጪ የዞኑ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት መምሪያ ምክትል ሀላፊ አቶ አዱኛ አዴሎ፣ በእጃችን ያለውን ሀብት ማየትና ማልማት ባለመቻላችን ብዙ ነገር እንዳጣን ስልጠናው አሳይቶናል ብለዋል።

ከዚህ ችግር በመውጣት ከአካባቢው ሀብት የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን ያሉ ጸጋዎችን ለይቶ ማልማት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሚፈለገውን ውጤት ለማስመዝገብና ለውጥ የታየባቸውንም ለማስቀጠል የሚችል የሰው ሀይል መፍጠር ላይ በትኩረት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

ስልጠናው በፈጠራና በፍጥነት እንዴት ውጤታማ ሥራ መስራት እንደሚቻል አቅም የገነቡበት መሆኑን የገለጹት ደግሞ የካፋ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ንጉሴ ባዩ ናቸው።  

በተጨማሪም በአካባቢ ያሉ ጸጋዎችን ለይቶ እንዴት ማልማት እንደሚቻልና ውጤታማነትን በማስቀጠል የህዝብንተጠቃሚነት ለማሳደግ ዕውቀት ማግኘታቸውንም ተናግረዋል።

ይህን መነሻ በማድረግም በቀጣይም በግብርና፣ በከተማ ልማት፣ በቱሪዝምና በሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች የተቀመጡ ግቦችን በማሳካት እምርታዊ ለውጥ ለማምጣት በቁጭት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም