የመደመር መንግሥት እይታ በክልሉ ያሉ የቱሪዝም ሀብቶችን በአግባቡ ለመጠቀም ምቹ ምህዳር ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግሥት እይታ በክልሉ ያሉ የቱሪዝም ሀብቶችን በአግባቡ ለመጠቀም ምቹ ምህዳር ፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 29/2018(ኢዜአ)፦ የመደመር መንግሥት እይታ በኦሮሚያ ክልል ያሉ የቱሪዝም ሀብቶችን በአግባቡ ለመጠቀም ምቹ ምህዳር መፍጠሩን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።
የዓለም ቱሪዝም ቀን በኦሮሚያ ክልል ደረጃ ለ21ኛጊዜ “ቱሪዝምና ዘላቂ ለውጥ” በሚል መሪ ሃሳብ በክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አዘጋጅነት በምሥራቅ ባሌ ዞን ጊኒር ከተማ ተከብሯል።
የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ሰለሞን ታምሩ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት በክልሉ ያሉ የቱሪዝም ሀብቶች ወደ ኢኮኖሚ ለመቀየር ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ተደርጓል።
የመደመር መንግሥት እይታ በክልሉ ያሉ የቱሪዝም ሃብቶችን በአግባቡ ለመጠቀም ምቹ ምህዳር መፍጠሩን ገልጸው፤በክልሉ ያሉ ሁሉም ወረዳዎች የራሳቸው የቱሪዝም መዳረሻ እንዲኖራቸው እየተሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት።
የምስራቅ ባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጃርሶ ቦሩና በበኩላቸው ዞኑ በርካታ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ሃብቶች እንዳሉት ተናግረዋል።
ለአብነትም የሶፍ ዑመር ዋሻ፣ ድሬ ሼህ ሁሴን፣ አስደናቂ መልክዓ ምድሮች እና ጥቅጥቅ አረንጓዴ አካባቢዎች እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።
ከዚህ ቀደም በአካባቢው የሚገኙትን ሃብቶች በማልማት ረገድ ምንም እንዳልተሰራ አንስተው፤ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በፌዴራልና በክልሉ መንግሥት ሰፋፊ መሠረተ ልማቶች በትኩረት እየተገነቡ መሆኑን ገልጸዋል።
በዞኑ የመንገድ፣ የመብራት፣ የቴሌኮም ኔትወርክን ጨምሮ ቱሪዝምን የሚያነቃቁ መሠረተ ልማቶች በመገንባታቸው ዞኑ ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆን መቻሉን ተናግረዋል።
መሠረተ ልማቶቹ በዞኑ ያሉ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ ማገዛቸውን አስታውቀዋል።