ቀጥታ፡

አዲሱ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስትራቴጂ በስራ ገበያው ተፈላጊና ብቃት ያለው  የሰው ኃይል ለማፍራት ያስችላል

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 29/2018 (ኢዜአ):-አዲሱ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስትራቴጂ  በስራ ገበያው ተፈላጊና ብቃት ያለው  የሰው ኃይል ለማፍራት እንደሚያስችል የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) ገለጹ።

የስራና ክህሎት ሚኒስቴር አዲሱን የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስትራቴጂ በተመለከተ ለክልሎች፣ ለከተማ አስተዳደሮችና ለዘርፉ አስፈጻሚ አካላት በቢሾፍቱ ከተማ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) በስልጠና ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ እንዳሉት፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በእውቀትና በክህሎት የበቃ የሰው ኃይል ማፍራት ያስፈልጋል።


 

ለዚህም ጠንካራ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማትን መገንባት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፥ ሚኒስቴሩ አዲስ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስትራቴጂ ማዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ስትራቴጂው ከዚህ ቀደም ከነበረው የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስትራቴጅ ትግበራ የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን መነሻ በማድረግ ከሀገር አቀፍ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ጋር እንዲጣጣም ተደርጎ መዘጋጀቱን ተናግረዋል። 

ስትራቴጂው በፍጥነት እየተለዋወጠ ካለው የስራ ገበያ ፍላጎት ጋር ብቁ ሆኖ ለመገኘት እና የወጣቱን እምቅ የፈጠራና የክህሎት አቅም አሟጦ ለመጠቀም የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት በፋይናንስ ራሳቸውን እንዲችሉ የሚያስችል በሂደትም ወደ ራስ ገዝነት የሚያሸጋግር መሆኑን አንስተዋል።


 

የቴክኒክና ሙያ ስልጠና አስተዳደርን በማጎልበት የስልጠና አግባብነትንና ጥራትን እንደሚያሻሽልና ለስራ ዝግጁ የሚያደርጉ ክህሎቶችን ለማዳበር እንደሚያግዝም እንዲሁ።

ስልጠናው በሀገር  አቀፍ ደረጃ ያሉ የዘርፉ ተቋማት በስትራቴጂው ላይ የጋራ ግንዛቤ ይዘው ለተግባራዊነቱ እንዲረባረቡ በማለም የተዘጋጀ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው አስገንዝበዋል።


 

በአርዳይታ ግብርና ኮሌጅ የስልጠና ዘርፍ ምክትል ዲን ነጅሃ ሐርዲን፤ አዲሱ ስትራቴጂ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማትን አሰራር የሚያዘመን ነው ብለዋል፡፡


 

ስትራቴጂው አዳዲስ እሳቤዎችን የያዘ እና ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የንፋስ ስልክ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዋና ዲን ሸለመ ንጉሴ ናቸው፡፡


 

የድሬዳዋ ኢትዮ-ጣሊያን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዋና ዲን ታደለ አሰፋ በበኩላቸው፤ አዲሱ ስትራቴጂ ስራ ፈጣሪ ትውልድ ለመገንባት ሁነኛ መፍትሔዎችን ይዞ መምጣቱን ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም