ቀጥታ፡

ለ4ኛው ዙር የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ዘመቻ  ውጤታማነት የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፉ ሚናውን ማጠናከር ይጠበቅበታል

ባሕርዳር፤ ሕዳር 29/2018(ኢዜአ) ፡-  በአማራ ክልል  4ኛው ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ውጤታማ  እንዲሆን  የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፉ  ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር ሚናውን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚጠበቅበት ተመላከተ። 

‎‎በክልሉ የሚካሄደውን 4ኛው ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻን አስመልክቶ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የንቅናቄ መድረክ ዛሬ በባሕርዳር ከተማ ተካሂዷል።


 

‎‎በመድረኩ ላይ የክልሉ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር  ስሜነህ አያሌው እንዳስታወቁት፤  የፖሊዮ ክትባት ዘመቻው ከታህሳስ 3 እስከ 6/2018 ዓ.ም በክልሉ በሁሉም ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች ይካሄዳል።

‎ክትባቱ የሚሰጠው ‎የፖሊዮ በሽታ ምልክት በመታየቱ እንደሆነ አንስተው፤ በሽታው  ህፃናትን ለሞትና ለአካል ጉዳት የሚዳርግ ተላላፊ በመሆኑ በመከላከል ለማጥፋት ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።

ከመደበኛው  ክትባት በተጨማሪ   ዕድሜያቸው ከ10 ዓመት በታች የሆኑ  ህፃናት  ከዚህ ቀደም ቢከተቡም ባይከተቡም  ክትባቱን እንዲወስዱ ይደረጋል ብለዋል።

‎ይህም ቤት ለቤት፣ በመጠለያ ጣቢያዎች፣ በትምህርት ቤት፣ በጤና ተቋማትና በጊዜያዊ የክትባት መስጫ ጣቢያዎች ተፈጻሚ እንደሚሆን አስረድተዋል። 


 

‎‎በዘመቻውም  የክትባት ቡድኖችና  አስተባባሪዎች እንደሚሳተፉ ጠቁመው፤ ለ‎ዘመቻው ውጤታማነት የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፉን ጨምሮ ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠርና ድጋፍ በማድረግ  ሚናቸውን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚጠበቅባቸው አመላክተዋል።

ወላጆችም ከ10 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት ልጆቻቸውን  በወቅቱ እንዲያስከትቡ ጥሪ አቅርበዋል። 

‎‎የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ  አበበ ተምትም  በበኩላቸው እንዳሉት፤  በክልሉ ተላላፊ በሽታዎችን አስቀድሞ በመከላከል ህፃናትን ከጉዳት ለመታደግ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።


 

‎‎በክልሉ 15 ዓይነት የክትባት አገልግሎቶችን በተሟላ መንገድ በመስጠት የህፃናትን ጤና ለመጠበቅ  ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል። 

‎‎የፖሊዮ በሽታን ለማጥፋት እየተደረገ ያለው ጥረት ስኬታማ እንዲሆን የሴክተር መስሪያ ቤቶች፣ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን እንዲሁም አጋር አካላት በቅንጅት በመስራት የድርሻቸውን እንዲወጡም  መልዕክት አስተላልፈዋል።

‎‎በንቅናቄው መድረክ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የወጣቶችና ሴት አደረጃጀቶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም