ቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ሊገነባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ሊገነባ ነው
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 29/2018(ኢዜአ)፦ ቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ አቅሙን የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችለውን የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ሊገነባ መሆኑን ገለጸ።
በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች ያሉ እምቅ ሃብቶችን በማልማት ምርታማነትን ማሳደግና ከተረጂነት የመውጣት እቅድ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል።
ክልሎችም የአደጋ ጊዜ ዝግጁነታቸውን በማረጋገጥ ለችግር በራስ አቅም ምላሽ መስጠት የሚያስችል የተቀናጀ አቅም በመገንባት ላይ ይገኛሉ።
የኦሮሚያ ክልልም ቡሳ ጎኖፋ የተሰኘ ተቋም አቋቁሞ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ችግሮችን ለመቋቋም እና አስቸኳይ ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም እየገነባ ይገኛል።
የክልሉ ቡሳ ጎኖፋ ምክትል ኃላፊ አቶ ተፈሪ በየነ፣ ተቋሙ ከአባላት መዋጮ ከሚያገኘው ገቢ እና የግብርና ስራዎችን በማከናወን አቅሙን ለማጠናከር በክልሉ የተለያዩ ዞኖች ላይ ሰብል የማልማት ስራ እያካሄደ ነው።
ይኸንኑ የግብርና ምርት በማቀነባበር ለሚፈለገው ዓላማ ለማዋል እንዲቻልም የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ሊገነባ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚሁ መሰረት ጉዳዩን የሚያስተባብር ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ተቋቁሞ የአዋጭነት ጥናት እና ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው ብለዋል።
በዚሁ መሰረት በቡልቡላ እና በነቀምቴ ግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚገነቡት ሁለት ፋብሪካዎች የተቋሙን ስራ የሚያሳልጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በቡልቡላ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሚገነባው ፋብሪካ በቀን ሁለት ሺህ ቶን ስንዴ የመፍጨት አቅም ያለው እና መኮሮኒና ፓስታንም የሚያቀነባብር መሆኑን አስረድተዋል።
በነቀምቴ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ደግሞ በምግብ እጦት ለተጎዱ ለአስቸኳይ ጊዜ የሚውል አጋዠ ምግብ የሚቀነባበር መሆኑን ተናግረዋል።
ፋብሪካዎቹ ቡሳ ጎኖፋ በራሱ አቅም የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፎችን ማድረግ እንዲችል የበለጠ አቅም የሚፈጥርለት መሆኑንም አውስተዋል።
ቡሳ ጎኖፋ ምርት ማምረት ብቻ ሳይሆን በቂ ማከመቻ መጋዘኖች ሊኖሩት እንደሚገባ ታምኖ በአዳማ እና ሻሸመኔ ከተሞች የራሱ መጋዘኖች ማዘጋጀቱንም አውስተዋል።
በቀጣይም በምስራቅ ባሌ ዞን ጊኒር ከተማ እንዲሁም በምስራቅ ወለጋ ዞን ነቀምቴ ከተማ ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ የመጋዘን ግንባታዎች ይከናወናሉ ብለዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን በሁሉም ዞኖች እና ወረዳዎች መጋዘን እንዲዘጋጅ አቅጣጫ መቀመጡንና ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።