ቀጥታ፡

ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በተሰሩ ስራዎች ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 29/2018(ኢዜአ)፦ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በተሰሩ ስራዎች ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ ገለጹ።

በስንዴ እና ቅባት እህሎች ልማት ላይ ያተኮረና ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።


 

በዚሁ ወቅት የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ እንዳሉት በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በግብርና ዘርፍ በተሰሩ ስራዎች ትልቅ ስኬት ተመዝግቧል።

በተለይ በኢኒሼቲቭ ደረጃ ልዩ ትኩረት በተሰጣቸው እንደ ስንዴና የቅባት እህሎች ባሉ ምርቶች ትልቅ እመርታ መገኘቱን አስታውቀዋል።

በዚህም ባለፉት ጥቂት ዓመታት የስንዴ ምርትና ምርታማነትን በእጅጉ በማሳደግ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ለውጪ ገበያ ማቅረብ መቻሉን ገልጸዋል።


 

በቅባት እህሎችም እንደ አኩሪ አተር፣ ሱፍ፣ ሰሊጥ እና ለውዝ ያሉ ምርቶች ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ ማደጉን ጠቁመዋል።

በግብርናው ዘርፍ ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን መተካት፣ ለአግሮ-ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ማቅረብና የስራ ዕድል መፍጠር የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

የስንዴ እና የቅባት እህሎችን ምርታማነት የበለጠ ውጤታማ ለማድረግና እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የባለድርሻ አካላት ትብብር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ስንዴ አምራቾችና ላኪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ሚሊዮን ቦጋለ እንዳሉት በስንዴ ምርት ላይ ውጤታማ የሆነው የሜካናይዜሽን ስራ በቅባት እህል በተጠናከረ መልኩ ሊተገበር ይገባል።


 

በዚህም ከቅባት እህል ጋር ተያይዞ ያሉት የአመራረት ዘዴዎችም በዘመናዊ መንገድ ቢጠናከሩ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ያስችላል ሲሉም ጠቁመዋል።

ሌላው አስተያየታቸውን የሰጡት የሙሉወርቅ ገበያው ዘይት ፋብሪካ ማኔጅንግ ዳይሬክተር ኢዮብ ወረታው ከገበያ ትስስር ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮች በዘላቂነት ሊፈቱ ይገባል ብለዋል።

በግብዓት አምራቾችና በፋብሪካዎች መካከል ያሉትን ህገወጥ የአቅርቦት ሰንሰለቶች ላይ ቁጥጥር በማድረግ ችግሩን መቅረፍ እንደሚገባ አንስተዋል።


 

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለሰ መኮንን(ዶ/ር)፥ ምርትና ምርታነማትን ለማሳደግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

መንግስት የፋይናንስ ተደራሽነትን እያረጋገጠና የመሰረተ ልማት ስራዎችን እያስፋፋ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሀሰን መሀመድ መንግስት የፖሊሲ ማሻሻያዎችን በማድረግና በኢንዱስትሪው ዘርፍ የነበሩ ተግዳሮቶችን በመፍታት ምርታማነትን ማሳደጉን ገልጸዋል።


 

የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም አጠቃቀም መሻሻሉን እንዲሁም በየደረጃው ያሉ የመንግስት አካላት የአምራች ኢንዱስትሪ ማነቆዎችን በመለየት የመፍታት ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ጠቁመዋል።

በዚህም ዘርፍ ተኪ ምርቶችን በማምረትና የወጪ ንግድ ምርቶችን በማስፋት የኢኮኖሚ ሽግግርን ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና እየተወጣ ነው ብለዋል።


 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም