የኢትዮጵያ ሰላማዊ የኒውክሌር ልማት መርኃ ግብር ከዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ማዕቀፎች ጋር በማጣጣም የሚተገበር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሰላማዊ የኒውክሌር ልማት መርኃ ግብር ከዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ማዕቀፎች ጋር በማጣጣም የሚተገበር ነው
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 29/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሰላማዊ የኒውክሌር ልማት መርኃ ግብር ከዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ማዕቀፎች ጋር በማጣጣም የሚተገበር መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያን የኒውክሌር ኃይል ልማት መርኃ ግብር ማስጀመሪያና የኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ኮሚሽን ሥራ ማስጀመሪያ የምክክር መድረክ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የሰው ልጆች ስልጣኔ ከእሳት፣ ውኃ፣ ነፋስና እንፋሎት የኃይል አማራጭ ልማት ጋር የተቆራኘ ነው።
የኃይል አቅርቦት የቴክኖሎጂ ግኝቶች ከኢኮኖሚ ልማት ጋር የተቆራኘ አስተማማኝና ተመጣጣኝ የማኅበረሰብ ዕድገት ለመፍጠር አቅም እንዳላቸው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያም በሰው ሰራሽ አስተውሎትና ቴክኖሎጂ ልማት በአዲስና አስፈላጊ የኢንዱስትሪ አብዮት ጉዞ ላይ እንደምትገኝ ተናግረዋል።
የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ልማት በአስተማማኝ፣ የረጅም ጊዜና ንጹህ የኃይል ምንጭነት ከፍተኛ ትኩረት እያገኘ መምጣቱን አንስተዋል።
የኒውክሌር ኃይል ለዘላቂ ብልጽግና መሠረት ነው ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትና ብዙ የሕዝብ ቁጥር የኃይል ፍላጎት ለማሟላት የረጅም ጊዜና ስትራቴጂካዊ የመሠረ ልማት ግንባታ ኢንቨስትመንቶችን ማስፋት አስፈላጊ ሆኗል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሰላማዊ የኒውክሌር ኃይል ልማት መርኃ ግብር በጤና፣ በግብርና እና በሌሎች የልማት መስኮች ትግበራ የኃይል ፍላጎትን በማሟላት ብልጽግናን የማረጋገጥ ትልም ያነገበ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የሰላማዊ ኒውክሌር ልማት መርሃ ግብርም የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ እውን የሚያደርግ ብሔራዊ የልማት ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪዎች፣ ዳታ ማዕከላት፣ ባቡሮችና ተሸከርካሪዎች እንደ ኒውክሌር ኃይል ባሉ ከታዳሽና አስተማማኝ የኃይል ምንጮች በሚገኝ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩባት ሀገር የማድረግ ጉዞም በወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ከዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋርም የኢትዮጵያን ብሔራዊ የኒውክሌር ልማት መርሃ ግብር የደህንነትና ግልጽነት ደረጃ ለማስጠበቅ እየተሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ልማት ውጥኗን ከጀመረች ማግስት አንስቶም የዓለም አቀፍ በአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ እየሰጠ ለሚገኘው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ሰላማዊ የኒውክሌር ልማት መርሃ ግብር ጠንካራ ትብብር ላይ በመመስረት ከዓለም አቀፍ መስፈርቶች፣ ደረጃዎችና የዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ማዕቀፎች ጋር ሙሉ በሙሉ በማጣጣም የሚተገበር መሆኑንም ተናግረዋል።
የአፍሪካ ኩራት የኢትዮጵያ የአቬሽን ኢንዱስትሪ እና የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬትም በሰላማዊ የኒውክሌር ኃይል አማራጭ ያላትን የብልጽግና ተምሳሌት ሕልም ለማሳካት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በመድረኩ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ የኒውክሌር ኢነርጂ ኮሚሽነር ሳንዶካን ደበበ፣ የዓለም አቀፍ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሚካኤል ቹዳኮቭና የባለድርሻ ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።