ኢትዮጵያ በሁሉም መመዘኛ ከጨለማ ወደ ንጋት እየተሸጋገረች ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በሁሉም መመዘኛ ከጨለማ ወደ ንጋት እየተሸጋገረች ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ህዳር 29/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በሁሉም መመዘኛ ከጨለማ ወደ ንጋት እየተሸጋገረች መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
20ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን "ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ እየተከበረ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጨምሮ ከፍተኛ የፌዴራል መንግሥት ሥራ ኃላፊዎች፣ የክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች በበዓሉ ላይ ተገኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ በአባቶቻችን ደም የወረስነውን ነጻነት በብልጽግና ማጽናት ከትውልዱ የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
ዛሬ ላይ ከተሞች እያደጉ የገጠር መንደሮች ለመሻገር በትጋት እየሰሩ ያሉበት ወቅት መሆኑን ገልጸው፤ ታሪካዊ ቅርሶችም አቧራቸውን አራግፈው የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ኩራት መሆናቸውን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ክረምት ከበጋ በማረስ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በሁሉም መመዘኛ ከጨለማ ወደ ንጋት እየተሸጋገረች መሆኑን ገልጸው፤ የወረስነውን ነጻነት ብቻ ሳይሆን የተሸከምነውን የትውልድ አደራ ማሰብ ይኖርብናል ብለዋል።
ብልጽግናን ማሳካት ፈታኝ ሂደት መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ችግሯን ብቻ ሳይሆን አቅሟን ማየት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ትውልዱ ኢትዮጵያ ችግሯን ብቻ ሳይሆን አቅሟን ፈልፍሎ የማየት እና የማውጣት አቅም እንዳለው በጅምር ስራዎች መታየቱን አንስተዋል።
በትብብር መንፈስ በብዙ ትጋት እና ልፋት አዲስ የታሪክ ገጽ መክፈት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ብልጽግና ምሉዕነት የሚረጋገጠው ኢትዮጵያውያን በህብረት መትጋት እና መስራት ሲችሉ መሆኑን አመልክተዋል።
መተባበርን፣ መከባበርን እና በጋራ መቆምን እንዲሁም ብሔራዊ ጥቅምን የሁላችን ሀብት እና ስንቅ ማድረግ አለብን ብለዋል።
የሀገርን መሻት እና የባዳን ክፋት መለየት እንደሚገባ ገልጸው፤ ኢትዮጵያውያን የባዳ ፍላጎት መሳሪያ መሆን እንደሌለባቸው ጠቁመዋል።
የሀገርን ጥቅምና የህዝብ ክብር ማስቀደም እንደሚገባ ገልጸው፤ ለዘመናዊነት እና ለውጥ ክፍት መሆን እንደሚገባም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ብዙ ተስፋ ያላት ሀገር መሆኗን ገልጸው፤ አስደናቂ ውጤት በማስመዝገብ እያንሰራራች ትገኛለች ብለዋል።
ይህን መልካም ጅማሮ ለማደናቀፍ ሙከራዎች መኖራቸውን ገልጸው፤ ማንኛውም ፈተና፣ ትንኮሳ እና ክፉ ሀሳብ የኢትዮጵያን ብልጽግና ማቆም አይችልም ብለዋል።