መንግስት ሁለንተናዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ ብዝኃነትን ከአንድነት ጋር የሚያስማማ መንገድ መርጦ በትኩረት እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ሁለንተናዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ ብዝኃነትን ከአንድነት ጋር የሚያስማማ መንገድ መርጦ በትኩረት እየሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 29/2018(ኢዜአ)፦ መንግስት ሁለንተናዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ብዝኃነትን ከአንድነት ጋር የሚያስማማ መንገድ መርጦ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።
20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት "ዲሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረ ብሄራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሐሳብ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ እየተከበረ ይገኛል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ባስተላለፉት መልዕክት፤ የኢትዮጵያ ብዝኃ ማንነት፣ ቋንቋ እና ባህል የሚገለጽበት ይህ በዓል በርካታ ዓላማዎችን አንግቦ እየተከበረ ይገኛል ብለዋል፡፡
ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እርስ በእርሳቸው እንዲተዋወቁ፣ ባህላቸውንና ልምዶቻቸውን እንዲለዋወጡ ብሎም ህብረ-ብሔራዊ አንድነታቸውን ማጠናከር ማስቻሉን ገልጸዋል።
የዘንድሮው በዓል ከቀደሙት የሚለየው "ዳግማዊ ዓድዋ" የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተመረቀበት እና የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ እውን ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያላቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች ጅማሮ በተበሰረበት ማግስት መከበሩ መሆኑንም አንስተዋል።
በህብረ ብሔራዊ አንድነት የደመቀ ብዝኃነታችንን ለዓለም ገልጸን የምናሳይበት ቀን ነው ያሉት አፈ-ጉባኤው፤ እውነተኛ የፌዴራል ሥርዓት በመገንባት ሂደት አዲስ የታሪክ እጥፋት ላይ መሆናችንን የምናስገነዝብበት ነው ብለዋል፡፡
ለብዝኃነት ክብር የሚሰጥ የጋራ ማንነት እንዲኖር መስራት ይገባል ያሉት አቶ አገኘሁ፤ የጋራ ማንነትን ለማጽናትና በብሔራዊነት ላይ የተመሰረተ አሰባሳቢ ትርክት መገንባት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
መንግስት ሁለንተናዊ ብልጽግናንን እውን ለማድረግ እና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ብዝኃነትን ከአንድነት ጋር የሚያስማማ መንገድ መርጦ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህንን እውን ከማድረግ አኳያም የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸውም ገልጸዋል፡፡