የበዓሉ መከበር የጋራ ትርክትን ለመገንባት እየተደረገ ያለውን የሀገራዊ ምክክር ሂደት ፍሬያማ ያደርገዋል- እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የበዓሉ መከበር የጋራ ትርክትን ለመገንባት እየተደረገ ያለውን የሀገራዊ ምክክር ሂደት ፍሬያማ ያደርገዋል- እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)
ሆሳዕና፤ ሕዳር 29/2018(ኢዜአ)፦የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል መከበር የጋራ ትርክትን ለመገንባት እየተደረገ ያለውን የሀገራዊ ምክክር ሂደት ፍሬያማ እንደሚያደርገው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለጹ።
20ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በሆሳዕና ከተማ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል፡፡
በበዓሉ ላይም የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ የበዓሉ መከበር የጋራ ትርክትን ለመገንባት እየተደረገ ያለውን የሀገራዊ ምክክር ሂደት ፍሬያማ ያደርገዋል።
በዓሉ የዳበረ ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር የሀገረ መንግሥት ግንባታን በማጠናከር ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ተናግረዋል፡፡
በዓሉ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ባህላዊ ትውፊቶቻቸውን ከመለዋወጥ በተጨማሪ የእርስ በእርስ ትስስርን ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል፡፡
በዓሉ የዘመናት ቁጭት ሆኖ የቆየውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በማጠናቀቅ ሌሎች አዳዲስ ፕሮጀክቶች በተጀመሩበት ማግስት መከበሩ የተለየ ያደርገዋል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የክልሉ ህዝብ ከሌሎች ህዝቦች ጋር በአብሮነት በመኖር የሚታወቅ ህዝብ መሆኑን ጠቅሰው ክልሉ ያለውን እምቅ አቅም በአግባቡ በመጠቀም ለሀገር ህልውና መጠበቅ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ተናግረዋል፡፡
በተያያዘም 21ኛው የብሄሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በኦሮሚያ ክልል ጅማ ከተማ እንደሚዘጋጅ የተጠቆመ ሲሆን በፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር እና በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ መካከል የሰንደቅ ዓላማ ርክክብ ተካሄዷል፡፡
በተመሳሳይም በበዓሉ አከባበር ስነ-ስርዓት ላይ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅን ተከትሎ የዋንጫ ርክክብ ስነ- ስርዓት ተካሄዷል፡፡
የዋንጫ ርክክቡን የታላቁ የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ለኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር አስረክበዋል፡፡