ባለፉት የለውጥ ዓመታት በዓሉ የህዝቦችን ህብረብሔራዊ አንድነትና አብሮ የመኖር እሴት በማጠናከር በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት የለውጥ ዓመታት በዓሉ የህዝቦችን ህብረብሔራዊ አንድነትና አብሮ የመኖር እሴት በማጠናከር በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 29/2018(ኢዜአ)፡- ባለፉት የለውጥ ዓመታት በዓሉ የህዝቦችን ህብረብሔራዊ አንድነትና አብሮ የመኖር እሴት በማጠናከር ዘላቂ ልማትና ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።
ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት በሚል መሪ ሃሳብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ እየተከበረ ይገኛል።
በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፤ ምክር ቤቱ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን እንዲከበር ሲወስን ብሔር ብሔረሰቦች አርስ በእርሳቸው እንዲተዋወቁ፤ ባህላዊ እሴቶቻቸውንና መልካም ልምድና ተሞክሮዋቻቸውን እንዲለዋወጡና ህብረብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለዘላቂ ሰላም ለሀገረ መንግስት ግንባታና ለልማት በጋራ እንዲቆሙ ማድረግም እንዲሁ፡፡
ባለፉት 19 ዓመታት በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት በተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች አስተናጋጅነት በዓሉ ሲከበር መቆየቱን ያስታወሱት አፈጉባዔው ይህም በህብረብሔራዊ አንድነት ላይ ውጤቶች እንዲመዘገቡ ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡
በተለይም ባለፉት የለውጥ ዓመታት የህዝቦችን ህብረብሔራዊ አንድነትና አብሮ የመኖር እሴት በማጠናከር የሀገረ መንግስት ግንባታውን እና ዘላቂ ልማትና ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉንም አውስተዋል፡፡
የዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የጋራ ትርክት ውጤት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተጠነቀቀበት ወቀት የሚከበር መሆኑና የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጉዞን እውን ማድረግ የሚየስችሉ ታላላቅ ፕሮጀክቶች በተጀመሩበት ወቅ የሚከበር መሆኑ ለየት ያደርገዋል ነው ያሉት፡፡
20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በህብረብሔራዊ አንድነት የደመቀ ብዝሀነትን ለዓለም ገልጸን የምናሳይበት ነው ያሉት አፈጉባዔው ሁሉም ማንነቶች እኩል የሚስተናገዱበት እውነተኛ የፌዴራል ስርዓት በመገንባት ሂደት አዲስ ታሪክ እጥፋት ላይ መሆናችንን የምናሳይበት ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ከኩስመና ዘመን ወደ ማንሰራራት፤ ከቁዘማ ወደ መነቃቃት፤ ከጨለማ ወደ ተስፋ ብርሃን የተሸጋገርን መሆኑን የምናሳይበት ነውም ብለዋል በመልዕክታቸው፡፡
ቀኑ በመከባበር፤ በመደጋገፍ፤ በእኩልነትና በአንድነት በመኖር በጋራ የመልማት ቃል ኪዳናችንን የምናድስበት ቀን ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
ይህንን የጋራ ኢትዮጵያዊ ማንነት ለማጽናትና የህዝቦች የዘመናት አብሮነት እንደተጠበቀ ለማዝለቅ በህብረ ብሔራዊነት ላይ የተመሰረተ አሰባሳቢ ትርክት መገንባት እንደሚያስፈልግም አብራርተዋል፡፡